ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 50:5-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ወደ ጽዮን የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ፤ፊታቸውንም ወደዚያ ያቀናሉ።መጥተውም ከቶ በማይረሳ፣በዘላለም ቃል ኪዳን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ይጣበቃሉ።

6. “ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤እረኞቻቸው አሳቷቸው፤በተራሮችም ላይ እንዲቅበዘበዙ አደረጓቸው፤በተራራና በኰረብታ ላይ ተንከራተቱ፤ማደሪያቸውንም ረሱ።

7. ያገኛቸው ሁሉ ይውጣቸዋል፤ጠላቶቻቸውም፣ ‘እኛ በደለኞች አይደለንም፤እነርሱ የአባቶቻቸውን ተስፋ እግዚአብሔርን፣እውነተኛ ማደሪያቸው የሆነውን እግዚአብሔርን በድለዋል’ አሉ።

8. “ከባቢሎን ሽሹ፤የባቢሎናውያንን ምድር ልቀቁ፤መንጋ እንደሚመራ የፍየል አውራ ሁኑ።

9. የታላላቅ መንግሥታትን ማኅበር፣ከሰሜን በባቢሎን ላይ አስነሣለሁ፤እነርሱም በእርሷ ላይ ይሰለፋሉ፤መጥተውም ይይዟታል።ቀስቶቻቸው ባዶ እጃቸውን እንደ ማይመለሱ፣እንደ ሥልጡን ተዋጊዎች ናቸው።

10. የባቢሎን ምድር ትዘረፋለች፤የሚዘርፏትም ሁሉ እስኪበቃቸው ይመዘብሩአታል፤”ይላል እግዚአብሔር።

11. “እናንተ ርስቴን የበዘበዛችሁ ሆይ፤ደስ ስላላችሁና ሐሤትም ስላደረጋችሁ፣በመስክ እንዳለች ጊደር ስለ ፈነጫችሁ፤እንደ ድንጒላ ፈረስ ስለ አሽካካችሁ፤

12. እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፤የወለደቻችሁም ትዋረዳለች።እርሷም ምድረ በዳ፣ ደረቅ ምድርና በረሓ፣ከመንግሥታትም ሁሉ ያነሰች ትሆናለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 50