ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 50:2-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. “በሕዝቦች መካከል ተናገሩ፤ አስታውቁም፤ሰንደቅ ዐላማ አንሡ፤ ዐውጁ፤አንዳች ሳታስቀሩ፣ እንዲህ በሉ፤‘ባቢሎን ትያዛለች፤ቤል ይዋረዳል፤ሜሮዳክ በሽብር ይሞላል፤ጣዖቶቿ ይዋረዳሉ፤አማልክቷም ይሸበራሉ።’

3. ከሰሜን አንድ መንግሥት መጥቶ ይወጋታል፤ምድሯንም ባድማ ያደርጋል፤የሚኖርባትም አይገኝም፤ሰዎችና እንስሳትም ሸሽተው ይሄዳሉ።

4. “በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜም፤”ይላል እግዚአብሔር፤“የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ በአንድነት ይመጣሉ፤አምላካቸውንም እግዚአብሔርን በመፈለግ እያለቀሱ ይመጣሉ።

5. ወደ ጽዮን የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ፤ፊታቸውንም ወደዚያ ያቀናሉ።መጥተውም ከቶ በማይረሳ፣በዘላለም ቃል ኪዳን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ይጣበቃሉ።

6. “ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤እረኞቻቸው አሳቷቸው፤በተራሮችም ላይ እንዲቅበዘበዙ አደረጓቸው፤በተራራና በኰረብታ ላይ ተንከራተቱ፤ማደሪያቸውንም ረሱ።

7. ያገኛቸው ሁሉ ይውጣቸዋል፤ጠላቶቻቸውም፣ ‘እኛ በደለኞች አይደለንም፤እነርሱ የአባቶቻቸውን ተስፋ እግዚአብሔርን፣እውነተኛ ማደሪያቸው የሆነውን እግዚአብሔርን በድለዋል’ አሉ።

8. “ከባቢሎን ሽሹ፤የባቢሎናውያንን ምድር ልቀቁ፤መንጋ እንደሚመራ የፍየል አውራ ሁኑ።

9. የታላላቅ መንግሥታትን ማኅበር፣ከሰሜን በባቢሎን ላይ አስነሣለሁ፤እነርሱም በእርሷ ላይ ይሰለፋሉ፤መጥተውም ይይዟታል።ቀስቶቻቸው ባዶ እጃቸውን እንደ ማይመለሱ፣እንደ ሥልጡን ተዋጊዎች ናቸው።

10. የባቢሎን ምድር ትዘረፋለች፤የሚዘርፏትም ሁሉ እስኪበቃቸው ይመዘብሩአታል፤”ይላል እግዚአብሔር።

11. “እናንተ ርስቴን የበዘበዛችሁ ሆይ፤ደስ ስላላችሁና ሐሤትም ስላደረጋችሁ፣በመስክ እንዳለች ጊደር ስለ ፈነጫችሁ፤እንደ ድንጒላ ፈረስ ስለ አሽካካችሁ፤

12. እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፤የወለደቻችሁም ትዋረዳለች።እርሷም ምድረ በዳ፣ ደረቅ ምድርና በረሓ፣ከመንግሥታትም ሁሉ ያነሰች ትሆናለች።

13. ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ፣የሚኖርባት አይገኝም፤በቍስሎችዋም ሁሉ ምክንያት፣በባቢሎን የሚያልፍ ሁሉ ይገረማል፤ ያፌዝባታልም።

14. “እናንተ ቀስት የምትገትሩ ሁሉ፣በባቢሎን ዙሪያ ተሰለፉ፤አንዳች ሳታስቀሩ ፍላጾችን ስደዱባት፤ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርታለችና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 50