ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 46:20-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. “ግብፅ ያማረች ጊደር ናት፣ነገር ግን ተናዳፊ ዝንብ፣ከሰሜን ይመጣባታል።

21. ቅጥረኞች ወታደሮቿም፣እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤የሚቀጡበት ጊዜ ስለ ደረሰ፣ጥፋታቸው ስለ ተቃረበ፣እነርሱም ወደ ኋላ ተመልሰው በአንድነት ይሸሻሉ፣በቦታቸውም ጸንተው ሊቋቋሙ አይችሉም።

22. ጠላት ገፍቶ ሲመጣባት፣ግብፅ እንደሚሸሽ እባብ ታፏጫለች፤ዛፍ እንደሚቈርጡ ሰዎች፣መጥረቢያ ይዘው ይመጡባታል።

23. ጥቅጥቅ ጫካ ቢሆንም፣ ደን ይመነጥራሉ፤”ይላል እግዚአብሔር፤“ብዛታቸው እንደ አንበጣ ነው፤ሊቈጠሩም አይችሉም።

24. የግብፅ ሴት ልጅ ለኀፍረት ትጋለጣለች፤ለሰሜን ሕዝብም ዐልፋ ትሰጣለች።”

25. የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በቴብስ አምላክ በአሞን ላይ፣ በፈርዖን ላይ፣ በግብፅና በአማልክቷ ላይ፣ በነገሥታቷም ላይ፤ እንዲሁም በፈርዖን በሚታመኑት ላይ ቅጣት አመጣለሁ፤

26. ነፍሳቸውን ለሚሹት ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆርና ለጦር መኰንኖቹ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ግብፅ እንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች” ይላል እግዚአብሔር።

27. “አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤እስራኤል ሆይ፤ አትሸበር፤አንተን ከሩቅ ስፍራ፣ዘርህንም ተማርኮ ከሄደበት ምድር አድናለሁ።ያዕቆብም ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፤የሚያስፈራውም አይኖርም።

28. አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤እኔ ከአንተ ጋር ነኝና” ይላል እግዚአብሔር፤“አንተን የበተንሁበትን ሕዝብ ሁሉ፣ፈጽሜ ባጠፋም እንኳ፣አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም።ተገቢውን ቅጣት እሰጥሃለሁ እንጂ፣ያለ ቅጣት አልተውህም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 46