ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 46:2-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ስለ ግብፅ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት በአራተኛው ዓመት በኤፍራጥስ ወንዝ በከርከሚሽ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ባሸነፈው በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ኒካዑ ሰራዊት ላይ የተነገረ መልእክት ይህ ነው፤

3. “ትልቁንና ትንሹን ጋሻ አዘጋጁ፤ለውጊያም ውጡ

4. ፈረሶችን ጫኑ፤በላያቸውም ተቀመጡ፤የራስ ቍር ደፍታችሁ፣በየቦታችሁ ቁሙ፤ጦራችሁን ወልውሉ፤ጥሩራችሁን ልበሱ

5. ነገር ግን ይህ የማየው ምንድ ነው?እጅግ ፈርተዋል፤ወደ ኋላ እያፈገፈጉ ነው፤ብርቱ ጦረኞቻቸው ተሸንፈዋል፤ዘወር ብለውም ሳያዩ፣በፍጥነት እየሸሹ ነው፤በየቦታውም ሽብር አለ፣”ይላል እግዚአብሔር።

6. “ፈጣኑ መሸሽ አይችልም፤ብርቱውም አያመልጥም፤በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ተሰናክለው ወደቁ።

7. “ይህ እንደ ዐባይ ወንዝ ሙላት የሚዘለው፣እንደ ደራሽ ወንዝ የሚፈሰው ማነው?

8. ግብፅ እንደ ዐባይ ወንዝ ሙላት ይዘላል፤እንደ ደራሽ ወንዝ ይወረወራል፤‘እወጣለሁ፤ ምድርንም እሸፍናለሁ፤ከተሞችንና ነዋሪዎቻቸውን አጠፋለሁ’ ይላል።

9. ፈረሶች ሆይ ዘላችሁ ውጡ ሠረገሎችም ሸምጥጡ፤ጋሻ ያነገባችሁ የኢትዮጵያና የፉጥ ሰዎች፣ቀስት የገተራችሁ የሉድ ጀግኖች፣እናንተ ብርቱ ጦረኞች ተነሥታችሁ ዝመቱ።

10. ያ ቀን ግን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን ነው፤ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን።ሰይፍ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ጥማቱም እስኪረካ ድረስ ደም ይጠጣል።በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጅቶአልና።

11. “ድንግሊቱ የግብፅ ሴት ልጅ ሆይ፤ወደ ገለዓድ ውጪ፤ የሚቀባ መድኀኒትም አምጪ፤ነገር ግን መድኀኒት የምታበዢው በከንቱ ነው፤ፈውስ አታገኚም።

12. ሕዝቦች ኀፍረትሽን ይሰማሉ፤ልቅሶሽም ምድርን ይሞላል።ጦረኛ በጦረኛው ይደናቀፋል፤ሁለቱም ተያይዘው ይወድቃሉ።”

13. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደናፆር መጥቶ ግብፅን እንደሚወጋ፣ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው መልእክት ይህ ነው፤

14. “ይህን በግብፅ ተናገር፤ በሚግዶልም አሰማ፤በሜምፎስና በጣፍናስም እንዲህ ብለህ ዐውጅ፤በቦታችሁ ቁሙ፤ ተዘጋጁም፤በዙሪያችሁ ያሉትን ሰይፍ ይበላቸዋልና።

15. ጦረኞችህ ለምን ተዘረሩ? እግዚአብሔር ገፍትሮ ስለሚጥላቸው መቆም አይችሉም።

16. ደጋግመው ይሰናከላሉ፣አንዱም በሌላው ላይ ይወድቃል፤‘ተነሡ እንሂድ፤ወደ ሕዛባችንና ወደ ትውልድ አገራችን እንመለስ፤ከጠላትም ሰይፍ እናምልጥ’ ይላሉ።

17. በዚያም የግብፅን ንጉሥ ፈርዖንን፣በተሰጠው ዕድል ያልተጠቀመ፣አለሁ አለሁ ባይ ደንፊ!’ ብለው ይጠሩታል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 46