ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 44:18-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ነገር ግን ለሰማይዋ ንግሥት ማጠንና የመጠጥ ቍርባን ማፍሰስ ከተውን ወዲህ፣ ሁሉን ነገር አጥተናል፤ በሰይፍና በራብም እያለቅን ነው።

19. ሴቶቹም፣ “ለሰማይዋ ንግሥት በምናጥንበትና የመጠጥ ቍርባን በምናፈስበት ጊዜ፣ በምስሏ ዕንጐቻ ስንጋግርና የመጠጥ ቍርባን ስናፈስላት ባሎቻችን አያውቁም ነበርን?” አሉ።

20. ኤርምያስ ይህን መልስ ለሰጠው ሕዝብ፣ ለወንዶችና ለሴቶች ሁሉ እንዲህ አለ፤

21. “እናንተና አባቶቻችሁ፣ ነገሥታታችሁና ባለሥ ልጣኖቻችሁ እንዲሁም የምድሪቱ ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ያጠናችሁትን እግዚአብሔር የማያስታው ሰውና የዘነጋው ይመስላችኋልን?

22. እግዚአብሔር ክፉ አድራጎታችሁንና አስጸያፊ ተግባራችሁን ሊታገሥ ባለመቻሉ፣ ዛሬ እንደሆነው ምድራችሁ የርግማን ምልክት፣ ሰው የማይኖርበት ባዶ ምድረ በዳ ሆኖአል።

23. ዕጣን በማጠን በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ስለ ሠራችሁና ቃሉን ስላልጠበቃችሁ ሕጉን፣ ሥርዐቱንና ትእዛዙን ስላላከበራችሁ ዛሬ እንደምታዩት ጥፋት መጥቶባችኋል።”

24. ኤርምያስም ለሕዝቡና ለሴቶቹ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “በግብፅ የምትኖሩ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

25. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እናንተና ሚስቶቻችሁ፣ ‘ለሰማይዋ ንግሥት ለማጠንና የመጠጥ ቍርባን ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለታችንን በእርግጥ እንፈጽማለን’ ብላችሁ የገባችሁትን ቃል በተግባር አሳይታችኋል።’“እንግዲያውስ ወደ ኋላ አትበሉ፤ ቃል የገባችሁትን፤ ስእለታችሁንም ፈጽሙ።

26. በግብፅ የምትኖሩ አይሁድ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ከእንግዲህ ወዲህ በየትኛውም የግብፅ ክፍል የሚኖር ማንኛውም አይሁዳዊ፣ ‘ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብሎ ስሜን እንዳይጠራ፣ እንዳይምልም በታላቁ ስሜ ምያለሁ፤

27. ለመልካም ሳይሆን ለክፉ እተጋባቸዋለሁና፤ በግብፅ የሚኖሩ አይሁድ ፈጽሞ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ይደመሰሳሉ።

28. ከሰይፍ አምልጠው፣ ከግብፅ ወደ ይሁዳ ምድር የሚመለሱት በጣም ጥቂት ሰዎች ይሆናሉ። በግብፅ ምድር ለመኖር የመጡት የይሁዳ ቅሬታ ሁሉ፣ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማንኛችን ቃል እንደሚጸና ያውቃሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 44