ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 44:10-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እስከ ዛሬ ድረስ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ክብርን አልሰጡኝም፤ በእናንተና በአባቶቻችሁ ፊት ያኖርሁትንም ሕጌንና ሥርዐቴን አልተከተሉም።’

11. “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእናንተ ላይ ጥፋት ለማምጣትና ይሁዳን ሁሉ ለመደምሰስ ቈርጬ ተነሥቻለሁ።

12. ሄደው በግብፅ ለመቀመጥ የወሰኑትን የይሁዳ ቅሬታዎች ሁሉ እነጥቃለሁ፤ ሁሉም ይጠፋሉ፤ በግብፅ ምድር በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በራብ ያልቃሉ፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ የመነቀፊያና የድንጋጤ፣ የመረገሚያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ።

13. ኢየሩሳሌምን እንደቀጣሁ፣ በግብፅ የሚኖሩትን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር እቀጣለሁ፤

14. ወደ ግብፅ የመጡት የይሁዳ ቅሬታዎች ወደ ይሁዳ ለመመለስ ቢመኙም ከጥቂት ስደተኞች በስተቀር አምልጦ ወይም ተርፎ ወደ ይሁዳ የሚመለስ አንድም ሰው አይኖርም።’ ”

15. ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ወንዶች ሁሉና በዚያ የነበሩት ሴቶች ሁሉ ይህም ማለት በሰሜንና በደቡብ ግብፅ የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ እንዲህ አሉት፤

16. “አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን መልእክት አንሰማም፤

17. እናደርጋለን ያልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ አባቶቻችን፣ ነገሥታታችንና ባለ ሥልጣኖቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ለሰማይዋ ንግሥት እናጥናለን፤ የመጠጥ ቍርባን እናፈስላታለን። በዚያን ጊዜ የተትረፈረፈ ምግብ ነበረን፤ በመልካም ሁኔታ እንገኝ ነበር እንጂ ምንም ክፉ ነገር አልገጠመንም።

18. ነገር ግን ለሰማይዋ ንግሥት ማጠንና የመጠጥ ቍርባን ማፍሰስ ከተውን ወዲህ፣ ሁሉን ነገር አጥተናል፤ በሰይፍና በራብም እያለቅን ነው።

19. ሴቶቹም፣ “ለሰማይዋ ንግሥት በምናጥንበትና የመጠጥ ቍርባን በምናፈስበት ጊዜ፣ በምስሏ ዕንጐቻ ስንጋግርና የመጠጥ ቍርባን ስናፈስላት ባሎቻችን አያውቁም ነበርን?” አሉ።

20. ኤርምያስ ይህን መልስ ለሰጠው ሕዝብ፣ ለወንዶችና ለሴቶች ሁሉ እንዲህ አለ፤

21. “እናንተና አባቶቻችሁ፣ ነገሥታታችሁና ባለሥ ልጣኖቻችሁ እንዲሁም የምድሪቱ ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ያጠናችሁትን እግዚአብሔር የማያስታው ሰውና የዘነጋው ይመስላችኋልን?

22. እግዚአብሔር ክፉ አድራጎታችሁንና አስጸያፊ ተግባራችሁን ሊታገሥ ባለመቻሉ፣ ዛሬ እንደሆነው ምድራችሁ የርግማን ምልክት፣ ሰው የማይኖርበት ባዶ ምድረ በዳ ሆኖአል።

23. ዕጣን በማጠን በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ስለ ሠራችሁና ቃሉን ስላልጠበቃችሁ ሕጉን፣ ሥርዐቱንና ትእዛዙን ስላላከበራችሁ ዛሬ እንደምታዩት ጥፋት መጥቶባችኋል።”

24. ኤርምያስም ለሕዝቡና ለሴቶቹ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “በግብፅ የምትኖሩ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 44