ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 36:21-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ንጉሡም ብራናውን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከው፤ ይሁዲም ከጸሓፊው ከኤሊሳማ ክፍል ብራናውን አምጥቶ፣ ለንጉሡና በንጉሡ አጠገብ ቆመው ለነበሩት መኳንንት ሁሉ አነበበላቸው።

22. ዘጠነኛው ወር እንደ መሆኑ፣ ንጉሡ የክረምትን ወራት በሚያሳልፍበት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ በምድጃ የሚነድ እሳትም ፊት ለፊቱ ነበር።

23. ይሁዲ ከብራናው ሦስት ወይም አራት ዐምድ ባነበበ ቍጥር ንጉሡ ብራናው ሁሉ እስከሚያልቅ ድረስ በጸሓፊ ቢላዋ እየቈረጠ እንዲቃጠል ወደ እሳቱ ምድጃ ይጥል ነበር።

24. ንጉሡም ሆነ ይህን ሁሉ ቃል የሰሙት መኳንንት ሁሉ አንዳች አልፈሩም፤ ልብሳቸውንም አልቀደዱም።

25. ኤልናታን፣ ድላያ፣ ገማርያም ንጉሡ ብራናውን እንዳያቃጥል ቢለምኑትም እንኳ አልሰማቸውም፣

26. ይልቁንም ጸሓፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይዘው ያስሩ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረምሕኤልን፣ የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያንና የአብድኤልን ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፤ እግዚአብሔር ግን ሰውሮአቸው ነበር።

27. ንጉሡ፣ ባሮክ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ የጻፈው ቃል ያለበትን ብራና ካቃጠለ በኋላ፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

28. “ሌላ ብራና ወስደህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው በመጀመሪያው ብራና ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ ጻፍበት፤

29. ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል፤ ይህቺን ምድር፣ በእርሷም ላይ የሚኖሩትን ሰዎችንና እንስሳትን ያጠፋል በማለት የጻፍህበት ለምንድን ነው?” ብለህ ብራናውን አቃጥለሃል።

30. ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፤ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ከዘሩ አይገኝም፤ ሬሳውም ወደ ውጭ ተጥሎ ለቀን ሐሩርና ለሌት ቍር ይጋለጣል።

31. እርሱንና ልጆቹን መኳንንቱንም ስለ ክፋታቸው እቀጣለሁ፤ አልሰሙኝምና አመጣባቸዋለሁ ያልሁትን ጥፋት ሁሉ በእነርሱና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት፣ በይሁዳም ሕዝብ ላይ አመጣለሁ።’ ”

32. ኤርምያስም ሌላ ብራና ወስዶ ለኔርያ ልጅ ለጸሓፊው ለባሮክ ሰጠው፤ ባሮክም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ባቃጠለው ብራና ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ ጻፈበት፤ ብዙ ተመሳሳይ ቃልም ተጨመረበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 36