ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 36:16-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እነርሱም ቃሉን ሁሉ በሰሙ ጊዜ እርስ በርሳቸው በፍርሀት በመተያየት ባሮክን፣ ይህን ሁሉ ቃል ለንጉሡ መንገር ይገባናል።” አሉት፤

17. ደግሞም፣ “ይህን ሁሉ እንዴት ልትጽፍ እንደ ቻልህ ንገረን፤ ኤርምያስ በቃል እየነገረህ ነውን?” ብለው ባሮክን ጠየቁት።

18. ባሮክም፣ “አዎን ይህን ሁሉ በቃሉ ነገረኝ፤ እኔም በብራናው ላይ በቀለም ጻፍሁ” ብሎ መለሰላቸው።

19. መኳንንቱም ባሮክን፣ “እንግዲያውስ አንተና ኤርምያስ ሄዳችሁ ተሸሸጉ፤ የት እንዳላችሁም ማንም አይወቅ” አሉት።

20. የብራናውን ጥቅልል በጸሓፊው በኤሊሳማ ክፍል ካስቀመጡት በኋላ፣ ንጉሡ ወዳለበት አደባባይ ሄደው የሆነውን ሁሉ ነገሩት።

21. ንጉሡም ብራናውን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከው፤ ይሁዲም ከጸሓፊው ከኤሊሳማ ክፍል ብራናውን አምጥቶ፣ ለንጉሡና በንጉሡ አጠገብ ቆመው ለነበሩት መኳንንት ሁሉ አነበበላቸው።

22. ዘጠነኛው ወር እንደ መሆኑ፣ ንጉሡ የክረምትን ወራት በሚያሳልፍበት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ በምድጃ የሚነድ እሳትም ፊት ለፊቱ ነበር።

23. ይሁዲ ከብራናው ሦስት ወይም አራት ዐምድ ባነበበ ቍጥር ንጉሡ ብራናው ሁሉ እስከሚያልቅ ድረስ በጸሓፊ ቢላዋ እየቈረጠ እንዲቃጠል ወደ እሳቱ ምድጃ ይጥል ነበር።

24. ንጉሡም ሆነ ይህን ሁሉ ቃል የሰሙት መኳንንት ሁሉ አንዳች አልፈሩም፤ ልብሳቸውንም አልቀደዱም።

25. ኤልናታን፣ ድላያ፣ ገማርያም ንጉሡ ብራናውን እንዳያቃጥል ቢለምኑትም እንኳ አልሰማቸውም፣

26. ይልቁንም ጸሓፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይዘው ያስሩ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረምሕኤልን፣ የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያንና የአብድኤልን ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፤ እግዚአብሔር ግን ሰውሮአቸው ነበር።

27. ንጉሡ፣ ባሮክ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ የጻፈው ቃል ያለበትን ብራና ካቃጠለ በኋላ፤ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

28. “ሌላ ብራና ወስደህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው በመጀመሪያው ብራና ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ ጻፍበት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 36