ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 36:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. የሳፋን ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ ከብራናው የተነበበውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ በሰማ ጊዜ፣

12. በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ጸሓፊው ክፍል ወረደ፤ በዚያም መኳንንቱ ሁሉ፦ ጸሓፊው ኤሊሳማ፣ የሸማያ ልጅ ድላያ፣ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፣ የሳፋን ልጅ ገማርያ፣ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ እንዲሁም ሌሎች መኳንንት ሁሉ ተቀምጠው ነበር።

13. ባሮክ ለሕዝቡ ከብራናው ሲያነብ ሚክያስ የሰማውን ሁሉ ከነገራቸው በኋላ፣

14. መኳንንቱ ሁሉ የኩሲን ልጅ የሴሌምያን ልጅ የናታንያን ልጅ ይሁዲን፣ “ለሕዝቡ ያነበብኸውን ብራና ይዘህ እንድትመጣ” ብለው ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርያም ልጅ ባሮክ ብራናውን ይዞ ወደ እነርሱ መጣ፤

15. እነርሱም፣ “እስቲ ተቀምጠህ አንብብልን” አሉት። ባሮክም አነበበላቸው፤

16. እነርሱም ቃሉን ሁሉ በሰሙ ጊዜ እርስ በርሳቸው በፍርሀት በመተያየት ባሮክን፣ ይህን ሁሉ ቃል ለንጉሡ መንገር ይገባናል።” አሉት፤

17. ደግሞም፣ “ይህን ሁሉ እንዴት ልትጽፍ እንደ ቻልህ ንገረን፤ ኤርምያስ በቃል እየነገረህ ነውን?” ብለው ባሮክን ጠየቁት።

18. ባሮክም፣ “አዎን ይህን ሁሉ በቃሉ ነገረኝ፤ እኔም በብራናው ላይ በቀለም ጻፍሁ” ብሎ መለሰላቸው።

19. መኳንንቱም ባሮክን፣ “እንግዲያውስ አንተና ኤርምያስ ሄዳችሁ ተሸሸጉ፤ የት እንዳላችሁም ማንም አይወቅ” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 36