ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 36:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ የነበረው ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤

2. “የብራና ጥቅልል ውሰድ፤ ለአንተም መናገር ከጀመርሁበት ከኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት አንሥቶ እስካሁን ድረስ ስለ እስራኤል፣ ስለ ይሁዳና ስለ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የነገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት፤

3. ምናልባትም የይሁዳ ሕዝብ ላመጣባቸው ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ ሲሰሙ፣ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ክፋታቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”

4. ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራው፤ ባሮክም እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ በብራናው ላይ ጻፈ።

5. ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ አለው፤ “እኔ ተከልክያለሁና ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት አልችልም፤

6. ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደህ፣ በቃል እየነገርሁህ በብራናው ላይ የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን ለተሰበሰበው ሕዝብ አንብብ፤ ከየከተሞቻቸው ለመጡት ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ አንብብ።

7. እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣና መቅሠፍት ታላቅ ስለ ሆነ፣ ምናልባት ልመናቸውን በእግዚአብሔር ፊት በማቅረብ እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።”

8. የኔርያ ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ የነገረውን ሁሉ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔርን ቃል ከብራናው አነበበ።

9. የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ የሆነው ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ሁሉና ከይሁዳ ከተሞች የመጡት ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ጾም ዐወጁ።

10. ባሮክም በብራና ላይ የተጻፈውን የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት በላይኛው አደባባይ፤ ‘አዲሱ በር’ በሚባለው በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ በሚገኘው በጸሓፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ክፍል ውስጥ ሆኖ ለሕዝቡ ሁሉ አነበበው።

11. የሳፋን ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ ከብራናው የተነበበውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ በሰማ ጊዜ፣

12. በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ጸሓፊው ክፍል ወረደ፤ በዚያም መኳንንቱ ሁሉ፦ ጸሓፊው ኤሊሳማ፣ የሸማያ ልጅ ድላያ፣ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፣ የሳፋን ልጅ ገማርያ፣ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ እንዲሁም ሌሎች መኳንንት ሁሉ ተቀምጠው ነበር።

13. ባሮክ ለሕዝቡ ከብራናው ሲያነብ ሚክያስ የሰማውን ሁሉ ከነገራቸው በኋላ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 36