ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 34:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው፤

7. በዚህም ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳ ከተሞች ለኪሶንና ዓዜቃን እየወጋ ነበር፤ ከተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችም የቀሩት እነዚሁ ብቻ ነበሩና።

8. ንጉሡ ሴዴቅያስ ባሪያዎችን ነጻ ለማውጣት ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።

9. እያንዳንዱ ሰው፣ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነችውን ሴት ባሪያውን ነጻ ማውጣት ነበረበት፤ ማንም ሰው አይሁዳዊ ወንድሙን በባርነት መግዛት አልነበረበትም።

10. በዚህ ቃል ኪዳን የተስማሙት ባለሥልጣኖችና ሕዝቡ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ባሪያዎቻቸውን ነጻ ለመልቀቅና ከእንግዲህ ባሪያ አድርገው ላይገዟቸው ተስማሙ።

11. በኋላ ግን ሐሳባቸውን ቀይረው ነጻ የለቀቋቸው ባሪያዎቻቸውን እንዲመለሱ አደረጓቸው፤ እንደ ገናም ባሪያ አድርገው ገዟቸው።

12. ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

13. “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በባርነት ከተገዙበት ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻችሁ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ፤

14. ‘ራሱን በባርነት ለእናንተ የሸጠውን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ በየሰባት ዓመቱ ነጻ ትለቃላችሁ፤ ስድስት ዓመት ከተገዛላችሁ በኋላ ነጻ ታወጡታላችሁ።’ አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም።

15. እናንተም አሁን ንስሓ በመግባት በፊቴ ትክክለኛ ነገር አደረጋችሁ፤ እያንዳንዳችሁም ለወገኖቻችሁ ነጻነት ዐወጃችሁ፤ ስሜ በሚጠራበት ቤትም በፊቴ ቃል ኪዳን ገባችሁ።

16. ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አረከሳችሁ፤ ወደ ፈለጉበት እንዲሄዱ ነጻ የለቀቃችኋቸውንም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቻችሁን መለሳችሁ፤ እንደ ገናም ባሪያዎቻችሁ አደረጋችኋቸው።

17. “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ለወንድሞቻችሁና ለወገኖቻችሁ ነጻነት አላወጃችሁምና አልታዘዛችሁኝም። እንግዲህ እኔ ‘ነጻነት’ ዐውጅላችኋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። ይኸውም በሰይፍ፣ በቸነፈርና በራብ የምትወድቁበት ‘ነጻነት’ ነው። ለምድር መንግሥታት ሁሉ መሠቀቂያ አደርጋችኋለሁ።

18. ኪዳኔን ያፈረሱትንና በፊቴ የገቡትን የኪዳኑን ቃል ያልፈጸሙትን ሰዎች ሥጋውን ሁለት ቦታ ከፍለው በመካከሉ እንዳለፉት፣ እንደ እንቦሳው አደርጋቸዋለሁ።

19. የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን መሪዎች፣ የቤተ መንግሥቱን ባለሟሎች፣ ካህናቱንና በእንቦሳው ሥጋ መካከል ያለፉትን ሕዝብ ሁሉ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 34