ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 34:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደናፆርና ሰራዊቱ ሁሉ፣ በግዛቱም ሥር ያሉ መንግሥታትና ሕዝቦች ሁሉ ኢየሩሳሌምንና በአካባቢዋ የሚገኙትን ከተሞች ይወጉ በነበረ ጊዜ፣ እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤

2. “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ ሄደህ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ ልሰጣት ነው፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል፤

3. አንተም በእርግጥ ትያዛለህ ዐልፈህም ለእርሱ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም። የባቢሎንን ንጉሥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ፊት ለፊትም ያነጋግርሃል፤ ወደ ባቢሎንም ትሄዳለህ።

4. “ ‘ነገር ግን፣ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፤ በሰይፍ አትሞትም፤

5. በሰላም ትሞታለህ። ሕዝቡ ከአንተ በፊት ለነበሩት ነገሥታት አባቶችህ ክብር በቀብራቸው ጊዜ እሳት እንዳነደዱ፣ በቀብርህም ጊዜ ስለ ክብርህ እሳት ያነዳሉ፤ “ዋይ ዋይ ጌታችን!” እያሉም ያለቅሱልሃል፤ እኔ ራሴ ይህን ቃል ተናግሬአለሁና፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”

6. ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው፤

7. በዚህም ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳ ከተሞች ለኪሶንና ዓዜቃን እየወጋ ነበር፤ ከተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችም የቀሩት እነዚሁ ብቻ ነበሩና።

8. ንጉሡ ሴዴቅያስ ባሪያዎችን ነጻ ለማውጣት ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።

9. እያንዳንዱ ሰው፣ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነችውን ሴት ባሪያውን ነጻ ማውጣት ነበረበት፤ ማንም ሰው አይሁዳዊ ወንድሙን በባርነት መግዛት አልነበረበትም።

10. በዚህ ቃል ኪዳን የተስማሙት ባለሥልጣኖችና ሕዝቡ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ባሪያዎቻቸውን ነጻ ለመልቀቅና ከእንግዲህ ባሪያ አድርገው ላይገዟቸው ተስማሙ።

11. በኋላ ግን ሐሳባቸውን ቀይረው ነጻ የለቀቋቸው ባሪያዎቻቸውን እንዲመለሱ አደረጓቸው፤ እንደ ገናም ባሪያ አድርገው ገዟቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 34