ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 33:10-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ይህችን ስፍራ፣ ‘ሰውና እንስሳት የማይኖሩባት ባድማ ናት’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን ሰውም ሆነ እንስሳ ባልነበሩባቸውና ባድማ በሆኑት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች፣ እንደ ገና ድምፅ ይሰማል፤

11. የሐሤትና የደስታ ድምፅ፣ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ እንዲሁም፦“እግዚአብሔር ቸር ነውና፤ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤”የሚል የምስጋናን መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡ ሰዎች ድምፅ ይሰማል፤ የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ እመልሳለሁና፤ ይላል እግዚአብሔር።

12. “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰውም ሆነ እንስሳት በማይኖሩበት በዚህ ባዶ ስፍራ፣ በከተማዎቹም ሁሉ እረኞች መንጎቻቸውን የሚያሳርፉበት እንደ ገና ያገኛሉ።

13. በተራራማው አገር፣ በምዕራብ ተራሮች ግርጌና በኔጌብ ባሉ ከተሞች በብንያም አገር፣ በይሁዳ ከተሞች እንዲሁም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ መንደሮች መንጎች እንደ ገና በሚቈጥራቸው ሰው እጅ ሥር ያልፋሉ’ ይላል እግዚአብሔር።

14. “ ‘ለእስራኤል ቤትና ለይሁዳ ቤት የገባሁትን የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል እግዚአብሔር።

15. “ ‘በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ከዳዊት ቤት ጻድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ፤በምድሪቱም ፍትሕንና ጽድቅን ያደርጋል።

16. በዚያ ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ኢየሩሳሌም በሰላም ትኖራለች፤የምትጠራበትም ስም፣“እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል።’

17. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ከዳዊት ዘር በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይታጣም፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 33