ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 31:21-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. “የጐዳና ምልክት አቁሚ፤መንገድ አመልካች ትከዪ፤የምትሄጂበትን መንገድ፣አውራ ጐዳናውን አስተውዪ፤ድንግሊቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሺ፤ወደ ከተሞችሽም ግቢ።

22. አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ይፈጥራል፤ሴት በወንድ ላይ ከበባ ታደርጋለች።

23. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኮአቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣ እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ።

24. ገበሬዎችና ዘላን ከብት አርቢዎች በይሁዳና በከተሞቿ በአንድነት ይኖራሉ።

25. የዛለችውን ነፍስ ዐድሳለሁ፤ የደከመችውንም አበረታለሁ።”

26. በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ነቅቼ ዙሪያዬን ተመለከትሁ፤ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆኖልኝ ነበር።

27. “እነሆ፤ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት” ይላል እግዚአብሔር፤ “በሰውና በእንስሳት ዘር የምሞላበት ጊዜ ይመጣል፤

28. ልነቅላቸውና ላፈርሳቸው፣ ልገለብጣቸውና ላጠፋቸው፣ መከራም ላመጣባቸው እንደ ተጋሁ ሁሉ፣ ላንጻቸውና ልተክላቸው ደግሞ እተጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

29. “በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ፣‘አባቶች በበሉት ጐምዛዛ የወይን ፍሬ፣የልጆች ጥርስ ጠረሰ’ የሚለውን ምሳሌ አይናገሩም።

30. ነገር ግን፣ እያንዳንዱ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል፤ ጐምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ የራሱን ጥርስ ይጠርሳል።

31. “ከእስራኤል ቤትና፣ከይሁዳ ቤት ጋር” ይላል እግዚአብሔር፤“አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት፣ጊዜ ይመጣል።

32. ከግብፅ አወጣቸው ዘንድ፣እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ኪዳንአይደለም፤የእነርሱ ባልገ ሆኜ ሳለሁ፣ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና።”ይላል እግዚአብሔር።

33. “ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤“ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤በልባቸውም እጽፈዋለሁ።እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።

34. ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣ሁሉም እኔን ያውቁኛልና፤”ይላል እግዚአብሔር።“በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም።”

35. በቀን እንድታበራ፣ፀሓይን የመደበ፣በሌሊት እንዲያበሩ፣ጨረቃንና ከዋክብትን ያዘዛቸው፣የሞገዱ ድምፅ እንዲተምም፣ባሕሩን የሚያናውጥ፣ስሙ የሰራዊት ጌታ የሆነ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

36. “ይህ ሥርዐት በፊቴ ከተሻረ፣”ይላል እግዚአብሔር፤“በዚያ ጊዜ የእስራኤልም ዘር በፊቴ፣መንግሥት መሆኑ ለዘላለም ይቀራል።”

37. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በላይ ያሉትን ሰማያትን መለካት፣በታችም ያሉትን የምድር መሠረቶች መመርመር ከተቻለ፣በዚያ ጊዜ የእስራኤልን ዘር ሁሉ፣ስላደረጉት ነገር ሁሉ እጥላቸዋለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 31