ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 31:2-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ፣በምድረ በዳ ሞገስን ያገኛል፤እኔም ለእስራኤል ዕረፍት ለመስጠት እመጣለሁ።”

3. እግዚአብሔር ከሩቅ ተገለጠልን፤ እንዲህም አለን፤“በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ስለዚህም በርኅራኄ ሳብሁሽ።

4. የእስራኤል ድንግል ሆይ፤ እንደ ገና አንጽሻለሁ፤አንቺም ትታነጪያለሽ፤ከበሮችሽንም እንደ ገና አንሥተሽ፣ከሚፈነጥዙት ጋር ትፈነድቂያለሽ።

5. እንደ ገናም በሰማርያ ኰረብቶች ላይ፣ወይን ትተክያለሽ፤አትክልተኞች ይተክሏቸዋል፤በፍሬውም ደስ ይላቸዋል።

6. ጠባቂዎች፣ በኤፍሬም ኰረብቶች ላይ፣‘ኑ፤ ወደ ጽዮን፣ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ!’ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣል።

7. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ፤ስለ ሕዝቦች አለቃ እልል በሉ፤ምስጋናችሁን አሰሙ፤‘እግዚአብሔር ሆይ፤ የእስራኤልን ቅሬታ፣ሕዝብህን አድን’ በሉ።

8. እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤በመካከላቸውም ዕውሮችና አንካሶች፣ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ።

9. እያለቀሱ ይመጣሉ፤እያጽናናሁ አመጣቸዋለሁ፤እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣ኤፍሬም በኵር ልጄ ነውና፣በውሃ ምንጭ ዳር፣በማይሰናከሉበት ቀና መንገድ እመራቸዋለሁ።

10. “ሕዝቦች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ሩቅ ባሉ የባሕር ጠረፎችም፣‘እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤መንጋውንም እንደ እረኛ ይጠብቃል’ ብላችሁ ዐውጁ።

11. እግዚአብሔር ያዕቆብን ይዋጀዋልና፤ከእርሱም ከሚበረቱት እጅ ይታደገዋልና።

12. መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በእግዚአብሔርም ልግስና፣በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤ከእንግዲህም አያዝኑም።

13. ኰረዶች ይዘፍናሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ጐረምሶችና ሽማግሌዎችም ይፈነጥዛሉ፤ልቅሶአቸውን ወደ ደስታ እለውጣለሁ፤ከሐዘናቸውም አጽናናቸዋለሁ፤ ደስታንም እሰጣቸዋለሁ።

14. ካህናቱን አትረፍርፌ እባርካለሁ፤ሕዝቤም በልግስናዬ ይጠግባል፤”ይላል እግዚአብሔር።

15. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ዋይታና መራራ ልቅሶ፣ከራማ ተሰማ፤ልጆቿ የሉምና፣ራሔል አለቀሰች፤መጽናናትም እንቢ አለች።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 31