ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 31:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. “የኤፍሬምን የሲቃ እንጒርጒሮ በእርግጥ ሰምቻለሁ፤‘እንዳልተገራ ወይፈን ቀጣኸኝ፤እኔም ተቀጣሁ።አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና፣መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ።

19. ከአንተ ከራቅሁ በኋላ፣ተመልሼ ተጸጸትሁ፤ባስተዋልሁም ጊዜ፣ጭኔን መታሁ፣የወጣትነት ውርደቴን ተሸክሜአለሁና፣ዐፈርሁ፤ ቀለልሁም።’

20. ኤፍሬም የምወደው፣ደስም የምሰኝበት ልጄ አይደለምን?ብዙ ጊዜ ተቃውሜው ብናገርም፣መልሼ ስለ እርሱ አስባለሁ፤አንጀቴ ይላወሳል፤በታላቅ ርኅራኄም እራራለታለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

21. “የጐዳና ምልክት አቁሚ፤መንገድ አመልካች ትከዪ፤የምትሄጂበትን መንገድ፣አውራ ጐዳናውን አስተውዪ፤ድንግሊቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሺ፤ወደ ከተሞችሽም ግቢ።

22. አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ይፈጥራል፤ሴት በወንድ ላይ ከበባ ታደርጋለች።

23. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኮአቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣ እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ።

24. ገበሬዎችና ዘላን ከብት አርቢዎች በይሁዳና በከተሞቿ በአንድነት ይኖራሉ።

25. የዛለችውን ነፍስ ዐድሳለሁ፤ የደከመችውንም አበረታለሁ።”

26. በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ነቅቼ ዙሪያዬን ተመለከትሁ፤ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆኖልኝ ነበር።

27. “እነሆ፤ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት” ይላል እግዚአብሔር፤ “በሰውና በእንስሳት ዘር የምሞላበት ጊዜ ይመጣል፤

28. ልነቅላቸውና ላፈርሳቸው፣ ልገለብጣቸውና ላጠፋቸው፣ መከራም ላመጣባቸው እንደ ተጋሁ ሁሉ፣ ላንጻቸውና ልተክላቸው ደግሞ እተጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

29. “በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ፣‘አባቶች በበሉት ጐምዛዛ የወይን ፍሬ፣የልጆች ጥርስ ጠረሰ’ የሚለውን ምሳሌ አይናገሩም።

30. ነገር ግን፣ እያንዳንዱ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል፤ ጐምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ የራሱን ጥርስ ይጠርሳል።

31. “ከእስራኤል ቤትና፣ከይሁዳ ቤት ጋር” ይላል እግዚአብሔር፤“አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት፣ጊዜ ይመጣል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 31