ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 31:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ድምፅሽን ከልቅሶ፣ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤”ይላል እግዚአብሔር።“ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤

17. ስለዚህ ወደ ፊት ተስፋ አለሽ”ይላል እግዚአብሔር።“ልጆችሽ ወደ ገዛ ምድራቸው ይመለሳሉ።

18. “የኤፍሬምን የሲቃ እንጒርጒሮ በእርግጥ ሰምቻለሁ፤‘እንዳልተገራ ወይፈን ቀጣኸኝ፤እኔም ተቀጣሁ።አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና፣መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ።

19. ከአንተ ከራቅሁ በኋላ፣ተመልሼ ተጸጸትሁ፤ባስተዋልሁም ጊዜ፣ጭኔን መታሁ፣የወጣትነት ውርደቴን ተሸክሜአለሁና፣ዐፈርሁ፤ ቀለልሁም።’

20. ኤፍሬም የምወደው፣ደስም የምሰኝበት ልጄ አይደለምን?ብዙ ጊዜ ተቃውሜው ብናገርም፣መልሼ ስለ እርሱ አስባለሁ፤አንጀቴ ይላወሳል፤በታላቅ ርኅራኄም እራራለታለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

21. “የጐዳና ምልክት አቁሚ፤መንገድ አመልካች ትከዪ፤የምትሄጂበትን መንገድ፣አውራ ጐዳናውን አስተውዪ፤ድንግሊቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሺ፤ወደ ከተሞችሽም ግቢ።

22. አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ይፈጥራል፤ሴት በወንድ ላይ ከበባ ታደርጋለች።

23. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኮአቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣ እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ።

24. ገበሬዎችና ዘላን ከብት አርቢዎች በይሁዳና በከተሞቿ በአንድነት ይኖራሉ።

25. የዛለችውን ነፍስ ዐድሳለሁ፤ የደከመችውንም አበረታለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 31