ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 29:17-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን፣ ራብንና መቅሠፍትን እሰድባቸዋለሁ፤ ከመበላሸቱ የተነሣም ሊበላ እንደማይቻል እንደ መጥፎ የበለስ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ።

18. በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት አሳድዳቸዋለሁ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉ አደርጋቸዋለሁ፤ በማሳድድባቸውም ሕዝቦች ዘንድ የርግማንና የድንጋጤ፣ የመሣቂያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ፤

19. በአገልጋዮቼ በነቢያት በኩል ደጋግሜ የላክሁላቸውን ቃሌን አልሰሙምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “እናንተ ምርኮኞችም አልሰማችሁም” ይላል እግዚአብሔር።

20. “ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

21. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚነግሯችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘እነዚህን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም ዐይናችሁ እያየ ይገድላቸዋል።

22. በእነርሱ ላይ ከደረሰው የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፣ “እግዚአብሔር፣ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግብህ” ብለው ይራገማሉ፤

23. ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ጋር በማመንዘርና ያልነገርኋቸውን ቃል በስሜ በሐሰት በመናገር በእስራኤል ዘንድ በደል ፈጽመዋልና። ይህንም እኔ ዐውቃለሁ፤ ምስክር ነኝ’ ” ይላል እግዚአብሔር።

24. “ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ ብለህ ንገረው፤

25. ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌም ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ ለካህኑ ለመዕሤያ ልጅ ለሶፎንያስና ለሌሎችም ካህናት ሁሉ በገዛ ስምህ ደብዳቤዎችን ልከሃል፤ ለሶፎን ያስም እንዲህ ብለሃል፤

26. “በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ምትክ ካህን አድርጎ ሾሞሃል፤ ነቢይ ነኝ እያለ ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ያበደ ሰው እግሩን በግንድ፣ ዐንገቱን በሰንሰለት መቀፍደድ ይገባሃል።

27. ታዲያ፣ ነቢይ ነኝ ባዩን የዓናቶቱን ኤርምያስን ለምን አልገሠጽኸውም?

28. ይህ ሰው፣ ‘የምርኮው ጊዜ ረዥም ስለ ሆነ፣ ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልትም ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ’ በማለት ወደ ባቢሎን መልእክት ልኮብናል።” ’ ”

29. ካህኑ ሶፎንያስም ደብዳቤውን ለነቢዩ ኤርምያስ አነበበለት።

30. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 29