ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 26:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ምናልባትም ሰምተው እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስላደረጉት ክፋት ላመጣባቸው ያሰብሁትን ቅጣት እተዋለሁ።

4. እንዲህም በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ባትሰሙኝና የሰጠኋችሁን ሕጌን ባትጠብቁ፣

5. ልትሰሟቸው ይገባ የነበረውን ወደ እናንተ ደጋግሜ የላክኋቸውን የአገልጋዮቼን የነቢያትን ቃል ባትሰሙ፣

6. ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርጋለሁ፤ ይህችንም ከተማ በምድር ሕዝብ ሁሉ ፊት የተረገመች አደርጋታለሁ።’ ”

7. ኤርምያስ ይህን ቃል በእግዚአብሔር ቤት ሲናገር፣ ካህናቱና ነቢያቱ፣ ሕዝቡም ሁሉ ሰሙ።

8. ነገር ግን ኤርምያስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሁሉ እንዲናገር ያዘዘውን ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፣ ካህናቱ፣ ነቢያቱና ሕዝቡም ሁሉ ይዘውት እንዲህ አሉ፤ “አንተ መገደል አለብህ!

9. ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፤ ይህቺም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ በእግዚአብሔር ስም ለምን ትንቢት ትናገራለህ?” ’ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተሰብስበው ኤርምያስን ከበቡት።

10. የይሁዳም ባለ ሥልጣኖች ስለ እነዚህ ነገሮች በሰሙ ጊዜ፣ ከቤተ መንግሥት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔር ቤት፣ ‘አዲሱ በር በተባለው መግቢያ ተቀመጡ።

11. ካህናቱና ነቢያቱም ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ፣ “በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁት ይህ ሰው በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ስለ ተናገረ ሞት ይገባዋል” አሉ።

12. ኤርምያስም፣ ለባለሥልጣኖቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የሰማችሁትን ሁሉ በዚህ ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እንድናገር እግዚአብሔር ልኮኛል።

13. አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታዘዙ። እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ለማምጣት የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል።

14. ስለ እኔ ከሆነ ግን እነሆ፤ በእጃችሁ ነኝ፤ መልካምና ተገቢ መስሎ የሚታያችሁን ሁሉ አድርጉብኝ።

15. ነገር ግን የሰማችሁትን ይህን ሁሉ ቃል በጆሮአችሁ እንድናገር እግዚአብሔር በእርግጥ ስለ ላከኝ ብትገድሉኝ፣ የንጹሕ ሰው ደም በማፍሰሳችሁ እናንተ ራሳችሁንና ይህቺን ከተማ፣ በውስጧም የሚኖረውን በደለኛ እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ።”

16. ባለሥልጣኖቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ “ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮአልና ሊገደል አይገባውም” አሉ።

17. ከአገሩ ሽማግሌዎችም አንዳንዶቹ ተነሥተው ለተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አሉ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 26