ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 26:15-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ነገር ግን የሰማችሁትን ይህን ሁሉ ቃል በጆሮአችሁ እንድናገር እግዚአብሔር በእርግጥ ስለ ላከኝ ብትገድሉኝ፣ የንጹሕ ሰው ደም በማፍሰሳችሁ እናንተ ራሳችሁንና ይህቺን ከተማ፣ በውስጧም የሚኖረውን በደለኛ እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ።”

16. ባለሥልጣኖቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ “ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮአልና ሊገደል አይገባውም” አሉ።

17. ከአገሩ ሽማግሌዎችም አንዳንዶቹ ተነሥተው ለተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አሉ፤

18. “ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን፣ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ጽዮን እንደ ዕርሻ ትታረሳለች፤ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤የቤተ መቅደሱም ተራራ፣ ዳዋ የወረሰው ኰረብታ ይሆናል።’

19. “ታዲያ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስም ሆነ የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ገደሉትን? ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን ፈርቶ ምሕረት አልለመነምን?’ እግዚአብሔርስ በእነርሱ ላይ ለማምጣት ያሰበውን ቅጣት አልተወምን? በራሳችን ላይ እኮ ታላቅ ጥፋት እያመጣን ነው።”

20. ደግሞም የቂርያትይዓሪም ሰው፣ የሸማያ ልጅ ኦርዮ፣ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ ሌላው ሰው ነበር፤ እርሱም እንደ ኤርምያስ በዚህች ከተማና በዚህ ምድር ላይ ትንቢት ተናግሮ ነበር።

21. ንጉሥ ኢዮአቄም፣ የጦር አለቆቹና ባለሥልጣኖቹ ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኦርዮም ይህን ሰምቶ በፍርሀት ወደ ግብፅ ሸሸ።

22. ይሁን እንጂ ንጉሥ ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንንና ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብፅ ላካቸው፤

23. እነርሱም ኦርዮን ከግብፅ አምጥተው፣ ወደ ንጉሥ ኢዮአቄም ወሰዱት፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው፤ ሬሳውንም ተራ ሰዎች በሚቀበሩበት ስፍራ ጣለው።

24. ነገር ግን የሳፋን ልጅ አኪቃም ከኤርምያስ ጐን ስለ ቆመ፣ ኤርምያስ ይገደል ዘንድ ለሕዝቡ ዐልፎ አልተሰጠም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 26