ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 25:25-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. የዘምሪ፣ የኤላምና የሜዶን ነገሥታትን ሁሉ፣

26. በቅርብና በሩቅ ያሉትን የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ በማከታተል፣ በምድር ላይ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ አጠጣኋቸው፤ ከእነዚህም ሁሉ በኋላ የሺሻክ ንጉሥ ደግሞ ይጠጣል።

27. “አንተም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠጡ፤ ስከሩ፤ አስታውኩም፤ ዳግመኛም ላትነሡ በመካከላችሁ በምሰደው ሰይፍ ፊት ውደቁ።’

28. ነገር ግን ጽዋውን ከእጅህ ለመውሰድና ለመጠጣት እንቢ ካሉ፣ እንዲህ በላቸው፦ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግድ ትጠጣላችሁ።

29. እነሆ፤ ስሜ የተጠራበትን ከተማ ማጥፋት እጀምራለሁ፤ ታዲያ ያለ ቅጣት ታመልጣላችሁን? ሳትቀጡ አትለቀቁም፤ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ሳትቀጡ አታመልጡም፤ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’

30. “እንግዲህ ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገርባቸው፤ እንዲህም በላቸው፣“ ‘እግዚአብሔር ከላይ ይጮኻል፤ከቅዱስ ማደሪያው ነጐድጓዳማ ድምፁን ያሰማል፤በራሱ ምድር ላይ እጅግ ይጮኻል፤እንደ ወይን ጨማቂዎች፣በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይም ያስገመግማል፤

31. እግዚአብሔር ከሕዝቦች ጋር ይፋረዳልና፣ታላቅ ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ያስተጋባል፤በሰው ሁሉ ላይ ፍርድን ያመጣል፤ክፉዎችንም ለሰይፍ ይዳርጋል”ይላል እግዚአብሔር።

32. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ ጥፋት፣ከአገር ወደ አገር እየተዛመተ መጥቶአል፤ብርቱ ዐውሎ ነፋስ፣ከምድር ዳርቻ ተነሥቶአል።

33. በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ፤ እንደ ጒድፍ በምድር ላይ ይጣላሉ እንጂ፣ አይለቀስላቸውም፤ ሬሳቸውም አይሰበሰብም፤ አይቀበርምም።

34. እናንት እረኞች፤ አልቅሱ፤ ዋይ በሉ፤እናንት የመንጋው ጌቶች፤ በዐመድ ላይ ተንከባለሉ፤የምትታረዱበት ቀን ደርሶአልና፤እንደ ውብ የሸክላ ዕቃ ወድቃችሁ ትከሰክሳላችሁ።

35. እረኞች የሚሸሹበት፣የመንጋ ጠባቂዎችም የሚያመልጡበት የለም።

36. እግዚአብሔር ማሰማሪያቸውን አጥፍቶአልና፣የእረኞችን ጩኸት፣የመንጋ ጠባቂዎችን ዋይታ ስሙ።

37. ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ፣ሰላማዊው ምድር ባድማ ይሆናል።

38. እንደ አንበሳ ከጐሬው ይወጣል፤ከአስጨናቂው ሰይፍ፣ከቍጣውም የተነሣ፣ምድራቸው ባድማ ትሆናለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 25