ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 25:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ይህም ማለት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያው ዓመት፣ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለኤርምያስ ቃል መጣለት፤

2. ስለዚህ ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩትም ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦

3. የይሁዳ ንጉሥ የአሞን ልጅ ኢዮስያስ ከነገሠበት ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሃያ ሦስት ዓመት ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ ደጋግሜም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም።

4. እግዚአብሔር አገልጋዮቹን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሞ ወደ እናንተ ላከ፤ ሆኖም አልሰማችሁም፤ ትኵረትም አልሰጣችሁትም።

5. እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እንግዲህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣት ምድር ለዘላለም ትቀመጣላችሁ።

6. ታገለግሏቸውና ታመልኳቸው ዘንድ ሌሎቹን አማልክት አትከተሉ፤ እጃችሁ በሠራው ነገር አታስቈጡኝ፤ እኔም ክፉ አላ ደርግባችሁም።”

7. “ነገር ግን አልሰማችሁኝም” ይላል እግዚአብሔር፤ ኋእጃችሁ በሠራው ነገር አስቈጣችሁኝ፤ በራሳችሁም ላይ ክፉ ነገር አመጣችሁ።”

8. ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃሌን ስላልሰማችሁ፣

9. የሰሜንን ሕዝብ ሁሉ፣ አገልጋዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ ሰዎች የሚጸየፉአቸውና የሚሣለቁባቸው፣ የዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ፤

10. የደስታንና የእልልታን ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ፣ የወፍጮን ድምፅና የመብራትን ብርሃን አስቀራለሁ።

11. አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።

12. “ነገር ግን ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣ የባቢሎንን ንጉሥና ሕዝቡን፣ የባቢሎናውያንንም ምድር ስለ በደላቸው እቀጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለዘላለምም ባድማ አደርጋታለሁ፤

13. በምድሪቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ ይኸውም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውንና ኤርምያስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ የተናገረውን ትንቢት አመጣባታለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 25