ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 2:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. እስራኤል ባሪያ ነውን? ወይስ የቤት ውልድ ባሪያ?ታዲያ፣ ስለ ምን ለብዝበዛ ተዳረገ?

15. አንበሶች በእርሱ ላይ አገሡ፤በኀይለኛ ድምፅም ጮኹበት።ምድሩን ባድማ አድርገውበታል፤ከተሞቹ ተቃጥለዋል፤ ወናም ሆነዋል።

16. ደግሞም የሜምፎስና የጣፍናስ ሰዎች፣መኻል ዐናትሽን ላጩሽ።

17. በመንገድ የሚመራሽን፣ እግዚአብሔር አምላክሽን በመተውሽ፣ይህን በራስሽ ላይ አላመጣሽምን?

18. ከሺሖር ወንዝ ውሃ ለመጠጣት፣አሁንስ ለምን ወደ ግብፅ ወረድሽ?ከኤፍራጥስ ወንዝስ ውሃ ለመጠጣት፣ወደ አሦር መውረድ ለምን አስፈለገሽ?

19. ክፋትሽ ቅጣት ያስከትልብሻል፤ክህደትሽም ተግሣጽ ያመጣብሻል፤ እግዚአብሔር አምላክሽን ስትተዪ፣እኔንም መፍራት ችላ ስትይ፣ምን ያህል ክፉና መራራ እንደሚሆንብሽ፣አስቢ፤ እስቲ አስተውዪ፤”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

20. “ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰበርሁ፤እስራትሽን በጣጠስሁ፤አንቺም፣ ‘አላገለግልህም’ አልሽ፤ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ሥር፣በያንዳንዱም ለምለም ዛፍ ሥር፣ለማመንዘር ተጋደምሽ።

21. እኔ፣ እንደ ምርጥ የወይን ተክል፣ጤናማና አስተማማኝ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ታዲያ ብልሹ የዱር ወይን ተክል ሆነሽ፣እንዴት ተለወጥሽብኝ?

22. በልዩ ቅጠል ብትታጠቢ፣ብዙ ሳሙና ብትጠቀሚም፣የበደልሽ ዕድፍ አሁንም በፊቴ ነው፤”ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

23. “ ‘አልረከስሁም፣በኣሊምን አልተከተልሁም’ እንዴት ትያለሽ?በሸለቆ ውስጥ ምን እንዳደረግሽእስቲ አስቢ፣ምንስ እንደ ፈጸምሽ ተገንዘቢ፤እንደምትፋንን ፈጣን ግመል ሆነሻል፤

24. በምድረ በዳ እንደ ለመደች፣በፍትወቷ ነፋስን እንደምታነፈንፍ፣ የሜዳ አህያ ነሽ፤ከመጎምጀቷ ማን ሊገታት ይችላል?ለሚፈልጓት ሁሉ ያለ ምንም ድካም፤በፍትወቷ ወራት በቀላሉ ትገኝላቸዋለች።

25. እግርሽ እስኪነቃ አትሩጪ፤ጉሮሮሽም በውሃ ጥም እስኪደርቅ አትቅበዝበዢ።አንቺ ግን፣ ‘በከንቱ አትድከም፤ባዕዳን አማልክትን ወድጃለሁ፤እነርሱን እከተላለሁ’ አልሽ።

26. “ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር፣የእስራኤልም ቤት አፍሮአል፤እነርሱ፣ ንጉሦቻቸውና ሹሞቻቸው፣ካህናታቸውና ነቢያታቸው እንዲሁ ያፍራሉ።

27. ዛፉን፣ ‘አንተ አባቴ ነህ’ድንጋዩንም፣ ‘አንተ ወለድኸኝ’ አሉ፤ፊታቸውን ሳይሆን፣ጀርባቸውን ሰጥተውኛልና፤በመከራቸው ጊዜ ግን፣‘መጥተህ አድነን’ ይላሉ።

28. ታዲያ፣ ልታመልካቸው ያበጀሃቸው አማልክት ወዴት ናቸው?በመከራህ ጊዜ ሊያድኑህ የሚችሉ ከሆነ፣ይሁዳ ሆይ፤ እስቲ ይምጡና ያድኑህ፤የከተሞችህን ቍጥር ያህል፣የአማልክትህም ብዛት እንዲሁ ነውና።

29. “ለምን በእኔ ታማርራላችሁ?ያመፃችሁብኝ እናንተ ሁላችሁ ናችሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 2