ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 19:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሄደህ፣ ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ፤ ከሕዝቡና ከካህናቱ መካከል ታላላቅ የሆኑትን አንዳንዶቹን ይዘህ፣

2. በገል በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ውጣ። በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፤

3. እንዲህም በል፤ ‘የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚዘገንን ክፉ ነገር እነሆ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ፤

4. እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤

5. እኔም ያላዘዝኋቸውን፣ ያልተናገርኋቸውን፣ ፈጽሞም ያላሰብሁትን፣ ወንዶች ልጆቻቸውን በእሳት ሊሠውለት ለበኣል መስገጃ ኰረብታዎች ሠርተዋል።

6. ስለዚህ ሰዎች ይህን ስፍራ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ብለው የማይጠሩበት ዘመን ይመጣል፤ ይላል እግዚአብሔር።

7. “ ‘በዚህ ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ዕቅድ አፈርሳለሁ፤ በጠላቶቻቸው ፊት ሕይወታቸውን በሚሹት እጅ በሰይፍ እንዲወድቁ አደርጋለሁ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ።

8. ይህችን ከተማ ድምጥማጧን አጠፋለሁ፤ ለመሣለቂያም አደርጋታለሁ፤ በዚያም የሚያልፉ ሁሉ ከደረሰባት ጒዳት የተነሣ ወይ ጒድ! ይላሉ ያሾፋሉም።

9. የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋለሁ፤ ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚሹ ጠላቶቻቸው ከበው ሲያስጨንቋቸው፣ አንዱ የሌላውን ሥጋ ይበላል።’

10. “ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 19