ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 18:3-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እኔም ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ወረድሁ፤ ሸክላውንም በመንኵ ራኩር ላይ ይሠራ ነበር።

4. ከጭቃ ይሠራው የነበረውም ሸክላ በእጁ ላይ ተበላሸ፤ ሸክላ ሠሪውም በሚፈልገው ሌላ ቅርጽ መልሶ አበጀው።

5. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤

6. “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ሸክላ ሠሪው እንደሚሠራው፣ እኔ በእናንተ ላይ መሥራት አይቻለኝምን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ጭቃው በሸክላ ሠሪው እጅ እንዳለ፣ እናንተም እንዲሁ በእጄ ውስጥ ናችሁ።

7. አንድ ሕዝብ ወይም መንግሥት እንዲነቀል፣ እንዲፈርስና እንዲጠፋ በተናገርሁ ጊዜ፣

8. ያስጠነቀቅሁት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፣ እኔ ላደርስበት ያሰብሁትን ክፉ ነገር እተዋለሁ።

9. በሌላም ጊዜ አንድን ሕዝብ ወይም መንግሥት አንጸውና እተክለው ዘንድ ተናግሬ፣

10. በፊቴ ክፉ ነገር ቢያደርግና ባይታዘዘኝ፣ አደርግለታለሁ ብዬ ያሰብሁትን መልካም ነገር አስቀርበታለሁ።

11. “አሁንም እንግዲህ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ጥፋትን እያዘጋጀሁላችሁ ነው፤ ክፋትንም እየጠነሰስሁላችሁ ነው። ስለዚህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ተግባራችሁን አቅኑ።” ’

12. እነርሱ ግን፣ ‘በከንቱ አትድከም፤ ባቀድነው እንገፋበታለን፤ እያንዳንዳችንም የክፉ ልባችንን እልኸኝነት እንከተላለን’ ይላሉ።”

13. ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እስቲ አሕዛብን፣‘እንዲህ ዐይነት ነገር በመካከላችሁ ተሰምቶ ያውቃል?’ ብላችሁ ጠይቁ።ድንግሊቱ እስራኤል፣እጅግ ክፉ ነገር አድርጋለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 18