ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 15:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ሙሴና ሳሙኤል እንኳ በፊቴ ቢቆሙ፣ ልቤ ለዚህ ሕዝብ አይራራምና፤ ከፊቴ አስወጣቸው፤ ይሂዱ።

2. እነርሱም፣ ‘ወዴት እንሂድ?’ ቢሉህ፣ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ለሞት የተመደበ ወደ ሞት፣ለሰይፍ የተመደበ ወደ ሰይፍ፣ለራብ የተመደበ ወደ ራብ፣ለምርኮ የተመደበ ወደ ምርኮ ይሄዳል።’

3. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አራት ዐይነት አጥፊዎችን እሰድባቸዋለሁ፤ እነዚህም፦ ለመግደል ሰይፍ፣ ለመጐተት ውሾች፣ እንዲሁም ጠራርጎ ለመብላትና ለማጥፋት የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ናቸው።

4. የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ካደረገው በደል የተነሣ፣ ለምድር ነገሥታት ሁሉ መሰቀቂያ አደርጋቸዋለሁ።

5. “ኢየሩሳሌም ሆይ፤ የሚራራልሽ ማን ነው?ማንስ ያለቅስልሻል?ደኅንነትሽንስ ማን ጎራ ብሎ ይጠይቃል?

6. እኔን ጥለሽኛል” ይላል እግዚአብሔር፤“ወደ ኋላም እያፈገፈግሽ ነው፤ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ አጠፋሻለሁም፤ከእንግዲህም አልራራልሽም።

7. በአገሪቱ የከተማ ደጆች፣በመንሽ እበትናቸዋለሁ፤ከመንገዳቸው አልተመለሱምና፣ሕዝቤን በሐዘን እመታለሁ፤ጥፋትም አመጣባቸዋለሁ፤

8. የመበለቶቻቸውን ቍጥር፣ከባሕር አሸዋ ይልቅ አበዛለሁ፤የጐበዛዝት እናቶች በሆኑትም ላይ፣አጥፊውን በቀትር አመጣባቸዋለሁ።ሽብርንና ድንጋጤን፣በድንገት አወርድባቸዋለሁ።

9. የሰባቶቹ እናት ትዝለፈለፋለች፤ትንፋሿም ይጠፋል፤ገና ቀን ሳለ ፀሓይዋ ትጠልቃለች፤እርሷም ታፍራለች፤ ትዋረዳለችም፤የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት፣ለሰይፍ እዳርጋቸዋለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 15