ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 40:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤እኔ እጠይቅሃለሁ፤አንተም መልስልኝ።

8. “ፍርዴን ታቃልላለህን?ወይስ አንተ ጻድቅ ለመሆን እኔን ትኰንናለህ?

9. እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን?ድምፅህስ እንደ እርሱ ድምፅ ሊያንጐደጒድ ይችላልን?

10. እንግዲያስ ክብርንና ልዕልናን ተጐናጸፍ፤ግርማ ሞገስንም ተላበስ፤

11. ቍጣህን አፍስስ፤ትዕቢተኛውን ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው፤

12. ትዕቢተኛውን ሰው ሁሉ ተመልክተህ ዝቅ አድርገው፤ክፉዎችንም በቆሙበት ስፍራ አድቅቃቸው።

13. ሁሉንም በአንድ ላይ ከዐፈር ደባልቃቸው፤ፊታቸውንም በመቃብር ውስጥ ሸፍን።

14. እኔም ቀኝ እጅህ እንደምታድንህ፣በዚያን ጊዜ አረጋግጬ እቀበላለሁ።

15. “አንተን እንደ ፈጠርሁ፣ የፈጠርሁትን፣‘ብሄሞት’ ተመልከት፤እንደ በሬ ሣር ይበላል፤

16. ብርታቱ ወገቡ ውስጥ፣ኀይሉም በሆዱ ጡንቻ ላይ ነው።

17. ጅራቱ እንደ ጥድ ዛፍ ይወዛወዛል፤የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።

18. ዐጥንቱ እንደ ናስ ቱቦ፣እጅና እግሮቹም እንደ ብረት ዘንግ ናቸው።

19. እርሱ የእግዚአብሔር ሥራ አውራ ነው፤በሰይፍ ሊቀርበውም የሚችል ፈጣሪው ብቻ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 40