ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 38:20-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ወደ ማደሪያቸው ልትወስዳቸው ትችላለህን?የመኖሪያቸውን መንገድ ታውቃለህ?

21. ያን ጊዜ ተወልደሃል! ዕድሜህ ትልቅ ነውና፣አንተስ በእርግጥ ሳታውቅ አትቀርም!

22. “ወደ በረዶው መጋዘን ገብተሃልን?የዐመዳዩንስ ማከማቻ አይተሃልን?

23. ይኸውም ለመከራ ጊዜ፣ለጦርነትና ለውጊያ ቀን ያስቀመጥሁት ነው።

24. መብረቅ ወደሚሰራጭበት ቦታ የሚያደርሰው መንገድ፣የምሥራቅም ነፋስ በምድር ላይ ወደሚበተንበት ስፍራ የሚወስደው የትኛው ነው?

25. ለዝናብ መውረጃን፣ለመብረቅም መንገድን ያበጀ ማን ነው?

26. በዚህም ማንም የማይኖርበትን ምድር፣ሰውም የሌለበትን ምድረ በዳ የሚያጠጣ፣

27. ባድማውንና በረሓውን መሬት የሚያጠግብ፣ሣርም እንዲበቅልበት የሚያደርግ ማን ነው?

28. ዝናብ አባት አለውን?የጤዛን ጠብታ ማን ወለደው?

29. በረዶ ከማን ማሕፀን ይወጣል?የሰማዩንስ ዐመዳይ ማን ይወልዳል?

30. ውሆች እንደ ድንጋይ ይጠነክራሉ፤የጥልቁ ገጽ እንደ በረዶ ይጋገራል።

31. “ፕልያዲስ የተባሉትን ውብ ከዋክብት ልትለጒም፣ወይም የኦርዮንን ማሰሪያ ልትፈታ ትችላለህን?

32. ማዛሮት የተባለውን የክዋክብት ክምችት በወቅቱ ልታወጣ፣ወይም ድብ የተባለውን ኮከብና ልጆቹን ልትመራ ትችላለህ?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 38