ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 37:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ልቤ በዚህ በኀይል ይመታል፤ከስፍራውም ዘለል ዘለል ይላል።

2. ስሙ! የድምፁን ጩኸት ስሙ፤ከአፉ የሚወጣውን ጒርምርምታ አድምጡ።

3. መብረቁን ከሰማይ ሁሉ በታች ያባርቃል፤ወደ ምድርም ዳርቻ ይልካል።

4. ከዚያም በኋላ የድምፁ ጩኸት ይመጣል፤በድምፁም ግርማ ያንጐደጒዳል፤ድምጹ በተሰማ ጊዜ፣መብረቁን የሚከለክል የለም።

5. የእግዚአብሔር ድምፅ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያንጐደጒዳል፤እኛ የማናስተውለውንም ታላቅ ነገር ያደርጋል።

6. በረዶውን፣ ‘በምድር ላይ ውደቅ’ውሽንፍሩንም ‘ዶፍህን አውርደው’ ይላል።

7. እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች ሁሉ ሥራውን ያውቁ ዘንድ፣እያንዳንዱ ሰው እንዳይሠራ ይገታዋል።

8. እንስሳት ይጠለላሉ፤በየዋሻቸውም ይቈያሉ።

9. ዐውሎ ነፋስ ከማደሪያው፣ብርድም ከብርቱ ነፋስ ይወጣል።

10. የእግዚአብሔር እስትንፋስ በረዶ ያስገኛል፤ሰፋፊ ውሆች ግግር በረዶ ይሆናሉ።

11. ደመናትን ርጥበት ያሸክማቸዋል፤መብረቁንም በውስጣቸው ይበትናል።

12. ያዘዘውን ለመፈጸም፣እርሱ በሚሰጠው መመሪያ፣በመላው የምድር ገጽ ላይ ይሽከረከራሉ።

13. ሰዎችን ለመቅጣት ደመና ያመጣል፤ወይም በዚሁ ምድሩን አጠጥቶ ፍቅሩን ይገልጻል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 37