ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 34:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እውነተኛ ብሆንም፣እንደ ውሸታም ተቈጥሬአለሁ፤በደል ባይኖርብኝም፣በማይፈወስ ቍስል ተመትቻለሁ።’

7. ፌዝን እንደ ውሃ የሚጠጣት፣እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?

8. ከክፉ አድራጊዎች ጋር ይተባበራል፤ከኀጢአተኞችም ጋር ግንባር ይፈጥራል።

9. ‘እግዚአብሔርን ለማስደሰት መሞከር፣ለሰው አንዳች አይጠቅምም’ ብሎአልና።

10. “ስለዚህ፣ እናንተ አስተዋዮች ስሙኝ፤ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ።

11. ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፤እንደ አካሄዱም ይከፍለዋል።

12. በእውነት እግዚአብሔር ክፋትን አይሠራም፤ሁሉን የሚችል አምላክ ፍትሕን አያጣምምም።

13. ምድርን እንዲገዛ የሾመው አለን?የዓለምስ ሁሉ ባለቤት ያደረገው ማን ነው?

14. እርሱ መንፈሱን መልሶ ቢወስድ፣እስትንፋሱንም ወደ ራሱ ቢሰበስብ፣

15. ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት በጠፋ፣ሰውም ወደ ዐፈር በተመለሰ ነበር።

16. “ማስተዋል ካለህ ይህን ስማ፤እኔ የምለውንም አድምጥ።

17. ፍትሕን የሚጠላ ሊያስተዳድር ይችላልን?አንተስ ጻድቁንና ኀያል የሆነውን ትኰንናለህ?

18. ነገሥታትን ‘የማትረቡ ናችሁ፣’መኳንንትንም፣ ‘ክፉዎች ናችሁ’የሚላቸው እርሱ አይደለምን?

19. ሁሉም የእጁ ሥራ ስለሆኑ፣እርሱ ለገዦች አያደላም፤ባለጠጋውንም ከድኻው አብልጦ አይመለከትም።

20. እነርሱም እኩለ ሌሊት ላይ በድንገት ይሞታሉ፤ሕዝብ ተንቀጥቅጦ ሕይወቱ ያልፋል፤ኀያላኑም የሰው እጅ ሳይነካቸው ይወገዳሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 34