ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 33:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጥሮኛል፤ሁሉን የሚችለውም አምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጥቶኛል።

5. የምትችል ከሆነ መልስልኝ፤ተዘጋጅተህም በፊቴ ቁም።

6. በእግዚአብሔር ፊት እኔም እንዳንተው ነኝ፤የተፈጠርሁትም ደግሞ ከዐፈር ነው።

7. እኔን መፍራት የለብህም፤እጄም ሊከብድብህ አይገባም።

8. “በእርግጥ የተናገርኸውን ሰምቻለሁ፤እንዲህም ስትል አድምጫለሁ፤

9. ‘ኀጢአት የሌለብኝ ንጹሕ ነኝ፤ከበደል ነጻ ነኝ፤ እድፈትም የለብኝም፤

10. እግዚአብሔር ግን ሰበብ ፈልጎብኛል፤እንደ ጠላቱም ቈጥሮኛል፤

11. እግሬን በግንድ አጣብቆአል፤እንቅስቃሴዬንም ሁሉ ይከታተላል።’

12. “ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰው ስለሚበልጥ፣ትክክል እንዳልሆንህ እነግርሃለሁ።

13. የሰውን አቤቱታ እንደማይሰማ፣ለምን ታማርርበታለህ?

14. ሰው ባያስተውለውም፣እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ይናገራል፤

15. ሰዎች ዐልጋቸው ላይ ተኝተው ሳሉ፣ከባድ እንቅልፍ ሲወድቅባቸው፣በሕልም፣ በሌሊትም ራእይ፣ ይናገራል።

16. በጆሯቸው ይናገራል፤በማስጠንቀቂያም ያስደነግጣቸዋል፤

17. ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሳል፤ከትዕቢት ይጠብቃል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 33