ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 32:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ስለዚህ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ እንዲህ አለ፤“እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፤እናንተ ግን አዛውንቶች ናችሁ፤ከዚህም የተነሣ የማውቀውን ለመናገር አልደፈርሁም፤ፈርቼ ዝም አልሁ።

7. ‘ዕድሜ ይናገራል፤ረጅም ዘመን ጥበብን ያስተምራል’ ብዬ ነበር።

8. ነገር ግን በሰው ያለው መንፈስ፣ሁሉን የሚችል አምላክ እስትንፋስ፣ማስተዋልን ይሰጣል።

9. ጠቢባን የሚሆኑት በዕድሜ የገፉ ብቻ አይደሉም፤የሚያስተውሉም ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም።

10. “ስለዚህ፣ ‘ስሙኝ፣እኔም የማውቀውን ልንገራችሁ’ እላለሁ።

11. እናንተ በምትነጋገሩበት ጊዜ ታገሥሁ፤ቃላት እየመረጣችሁ ስትናገሩ፣በጥሞና ሰማኋችሁ፤

12. በሙሉ ልብ አዳመጥኋችሁ፤ነገር ግን ከእናንተ የኢዮብን ቃል ያስተባበለ ማንም የለም፤ለንግግሩም አጸፋ የመለሰ አልተገኘም።

13. ‘እኛ ጥበብ አግኝተናል፤ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ይርታው’ አትበሉ።

14. ኢዮብ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልሰነዘረም፤እኔም እንደ እናንተ አነጋገር መልስ አልሰጠውም።

15. “እነርሱ ተስፋ ቈርጠው፤ የሚሉት የላቸውም፤የሚናገሩትም ጠፍቶአቸዋል።

16. እንግዲህ እነርሱ መልስ ስላጡ፣ጸጥ ብለውም ስለ ቆሙ፣ በትዕግሥት ልጠብቅን?

17. እኔም የምለው ይኖረኛል፤የማውቀውንም እገልጣለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 32