ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢዮብ 28:12-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “ነገር ግን ጥበብ ከወዴት ትገኛለች?ማስተዋልስ መኖሪያዋ የት ነው?

13. ሰው ዋጋዋን አያውቅም፤በሕያዋንም ምድር አትገኝም።

14. ውቅያኖስ፣ ‘በእኔ ውስጥ የለችም’ ይላል፤ባሕርም፣ ‘በእኔ ዘንድ አይደለችም’ ይላል።

15. ንጹሕ ወርቅ ሊገዛት አይችልም፤ዋጋዋም በብር አይመዘንም።

16. በኦፊር ወርቅ፣በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።

17. ወርቅም ብርሌም አይወዳደሯትም፤በወርቅ ጌጥም አትለወጥም።

18. ዛጐልና አልማዝ ከቍጥር አይገቡም፤የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍም ይበልጣል።

19. የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን ሊስተካከላት አይችልም፤ዋጋዋም በንጹሕ ወርቅ አይተመንም።

20. “ታዲያ፣ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች?ማስተዋልስ የት ትገኛለች?

21. ከሕያዋን ፍጥረታት ዐይን ሁሉ ተሰውራለች፤ከሰማይ ወፎችም ተሸሽጋለች።

22. ጥፋትና ሞት፣‘ወሬዋን ብቻ ሰማን’ ይላሉ።

23. ወደ እርሷ የሚወስደውን መንገድ የሚረዳ፣መኖሪያዋንም የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤

24. እርሱ የምድርን ዳርቻ ይመለከታልና፤ከሰማይ በታች ያለውንም ሁሉ ያያል።

25. ለነፋስ ኀይልን በሰጠ ጊዜ፣የውሆችን መጠን በለካ ጊዜ፣

26. ለዝናብ ሥርዐትን፣ለነጐድጓድም መንገድን ባበጀ ጊዜ፣

27. በዚያን ጊዜ ጥበብን ተመለከታት፤ ገመገማትም፤አጸናት፤ መረመራትም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢዮብ 28