ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 9:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. እነዚህ የወይን ጠጅ አቍማዳዎቻችን ያን ጊዜ ስንሞላቸው አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን እንዴት እንደተ ቀዳደዱ ተመልከቱ፤ ልብሳችንና ጫማችንም ብዙ መንገድ በመጓዛችን አልቀዋል።”

14. የእስራኤልም ሰዎች ከስንቃችው ላይ ጥቂት ወሰዱ፤ ስለ ጒዳዩ ግን እግዚአብሔርን አልጠየቁም ነበር።

15. ኢያሱም በሰላም ለመኖር የሚያስችላቸውን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ የጉባኤውም መሪዎች ይህንኑ በመሓላ አጸኑላቸው።

16. እስራኤላውያን ከገባዖን ሰዎች ጋር ቃል ኪዳኑን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ፣ ሰዎቹ እዚያው አጠገባቸው የሚኖሩ ጎረቤቶቻቸው መሆናቸውን ሰሙ።

17. ስለዚህ እስራኤላውያን ተጒዘው በሦስተኛው ቀን ገባዖን፣ ከፊራ፣ ብኤሮትና ቂርያትይዓይሪም ወደተባሉት የገባዖን ሰዎች ወደሚኖሩባቸው ከተሞች መጡ።

18. ሆኖም እስራኤላውያን አልወጓቸውም፤ የጉባዔው መሪዎች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ምለውላቸው ነበርና።ማኅበሩም ሁሉ በመሪዎቹ ላይ አጒረመረሙ፤

19. ነገር ግን መሪዎቹ ሁሉ ለማኅበሩ እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ ‘በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ስለማልንላቸው፣ አሁን ጒዳት ልናደርስባቸው አንችልም፤

20. እንዲህ እናደርግላቸዋለን፤ የገባንላቸውን መሓላ በማፍረስ ቊጣ እንዳይደርስብን፣ በሕይወት እንዲኖሩ እንዲሁ እንተዋቸዋለን፤

21. ነገር ግን ለማኅበረ ሰቡ በሙሉ ዕንጨት እየቈረጡ ውሃ እየቀዱ ይኑሩ።” ስለዚህ መሪዎቹ የገቡላቸው ቃል ተጠበቀ።

22. ከዚያም ኢያሱ የገባዖንን ሰዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እዚሁ አጠገባችን መኖራችሁ የታወቀ ሆኖ ሳለ፣ ‘የምንኖረው ከእናንተ በራቀ ስፍራ ነው’ ብላችሁ ያታለላችሁን ለምንድን ነው?

23. ስለዚህ አሁን የተረገማችሁ ናችሁ፤ ጥቂቶቻችሁም ለአምላኬ ቤት ምንጊዜም ዕንጨት ቈራጭ፣ ውሃ ቀጂ ባሮች ትሆናላችሁ።”

24. እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት፤ “አምላክህ እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው፣ ምድሪቱን በሙሉ ለእናንተ እንደሚሰጣችሁና ነዋሪዎቿንም ከፊታችሁ እንደሚያጠፋቸው በእርግጥ ለእኛ ለባሪያዎችህ ተነግሮናል፤ ስለዚህ ከእናንተ የተነሣ ለሕይወታችን በመሥጋት ይህን አድርገናል።

25. እነሆ፤ አሁን በእጅህ ውስጥ ነን፤ በጎና ትክክል መስሎ የታየህን ነገር ሁሉ አድርግብን።”

26. ስለዚህ ኢያሱ የገባዖንን ሰዎች ከእስራኤላውያን እጅ አዳናቸው፤ እነርሱም አልገደሏቸውም።

27. በዚያችም ዕለት ኢያሱ የገባዖንን ሰዎች ለማኅበረ ሰቡና እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ ለሚቆመው የእግዚአብሔር ለሆነው መሠዊያ እስከ ዛሬ ድረስ ዕንጨት ቈራጮችና ውሃ ቀጂዎች አደረጋቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 9