ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 4:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ይህም በመካከላችሁ ምልክት እንዲሆናችሁ ነው። ወደ ፊት ልጆቻችሁ፣ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው ቢጠይቋችሁ፣

7. የዮርዳኖስ ወንዝ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት መቆሙን፤ እንዲሁም ታቦቱ ዮርዳኖስን በሚሻገርበት ጊዜ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መቆሙን፣ እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ሕዝብ የዘላለም መታሰቢያ መሆናቸውን ንገሯቸው።”

8. እስራኤላውያንም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረውም መሠረት፣ በእስራኤል ነገዶች ቊጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል አነሡ፤ ወደ ሰፈራቸውም ይዘው በመሻገር በዚያ አኖሯቸው።

9. ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ቆመውበት በነበረው በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ሌሎች ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን አቆመ፤ እነዚህም ድንጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ በዚሁ ስፍራ ይገኛሉ።

10. ሙሴ ለኢያሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት፣ እግዚእብሔር ለሕዝቡ እንUntitled eventዲነግር ኢያሱን ያዘዘው እስኪፈጸም ድረስ፣ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ቈዩ፤ ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ፤

11. ሕዝቡ ሁሉ ተሻግረው እንዳበቁ፣ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ፣ ሕዝቡ እያዩአቸው ተሻገሩ።

12. የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ፣ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእስራኤላውያን ፊት ቀድመው ተሻገሩ።

13. አርባ ሺህ ያህሉ ጦርና ጋሻቸውን ይዘው፣ ለውጊያ ዝግጁ ሆነው፣ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ።

14. በዚያች ዕለት እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤ ሕዝቡ ሙሴን እንዳከበሩት ሁሉ፣ ኢያሱንም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አከበሩት።

15. ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤

16. “የምስክሩን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ እዘዛቸው።”

17. ኢያሱም ካህናቱን “ከዮርዳኖስ ውጡ” ብሎ አዘዛቸው።

18. ካህናቱ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ከውሃው በመውጣት እግራቸው ደረቁን መሬት ልክ ሲነካ የዮርዳኖስ ውሃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፤ እንደ ቀድሞው ሁሉ ሞልቶ በዳሩ ሁሉ ይፈስ ጀመር።

19. የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ሕዝቡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ በኢያሪኮ ምሥራቃዊ ዳርቻ በጌልገላ ሰፈረ።

20. ኢያሱም ከዮርዳኖስ ወንዝ ያወጧቸውን ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች በጌልገላ ተከላቸው፤

21. እስራኤላውያንንም እንዲህ አላቸው፤ “ልጆቻችሁ ወደ ፊት፣ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው አባቶቻቸውን ቢጠይቁ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 4