ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 24:13-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ፤ እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’

14. “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብፅ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ።

15. እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”

16. ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ።

17. እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብፅ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጒዞአችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው።

18. እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።”

19. ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ እርሱ ቅዱስ አምላክና፤ ቀናተኛም አምላክ ነው፤ ዐመፃችሁን ወይም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም።

20. እግዚአብሔርን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን የምታመልኩ ከሆነ፣ መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችኋልም።”

21. ሕዝቡ ግን ኢያሱን፣ “የለም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 24