ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 15:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከይሁዳ ድርሻ ላይ ከፍሎ ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ሰጠው፤ አርባቅም የዔናቅ አባት ነበረ።

14. ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ዘሮች ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ከኬብሮን አሳደዳቸው፤

15. ከዚያም በዳቤር ሕዝብ ላይ ዘመተ፤ ዳቤር ቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበር።

16. ካሌብ፣ “ቂርያትሤፍርን ወግቶ ለሚይዝ ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ።

17. ስለዚህ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዛት፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳን ዳረለት።

18. ዓክሳ ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜም፣ ከአባትዋ ላይ የእርሻ መሬት እንዲለምን አጥብቃ ነገረችው። ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች ካሌብ፣ “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።

19. እርስዋም፣ “እባክህ፤ በጎ ነገር አድርግልኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ጉድጓዶች ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 15