ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 13:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢያሱ በሸመገለና ዕድሜው በገፋ ጊዜ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ አርጅተሃል፤ ዕድሜህም ገፍቶአል፤ ነገር ግን መያዝ ያለበት እጅግ በጣም ሰፊ ምድር ገና አለ።

2. “የሚቀረውም ምድር ይህ ነው፤ እርሱም የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ ነው፤

3. ከግብፅ በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ከሺሖር ወንዝ አንሥቶ፣ በሰሜን እስከ አቃሮን ወሰን ያለው አገር፣ ሁሉም እንደ ከነዓናውያን ምድር ይቈጠራል፤ ይኸውም በጋዛ፣ በአሽዶድ፣ በአስቀሎና፣ በጌትና በአቃሮን የሚኖሩትን የአምስቱን የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምድር የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም የኤዋውያን ምድር ነበር።

4. በደቡብ በኩል የከነዓናውያን ምድር ሁሉና የሲዶናውያን ይዞታ ከሆነችው ከመዓራ አንሥቶ እስከ አፌቅ ያለው የአሞራውያን ግዛት፣

5. የጌባላውያንም ምድር፤ በምሥራቅም ከበኣልጋድ አንሥቶ በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ አልፎ፣ እስከ ሐማት መተላለፊያ ያለው የሊባኖስ ምድር ሁሉ ነው።

6. “ከሊባኖስ እስከ ማሴሮን ባለው ተራራማ ምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሲዶናውያንንም ጭምር እኔው ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አሳድጄ አስወጣቸዋለሁ። ብቻ አንተ ባዘዝሁህ መሠረት ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለእስራኤላውያን አካፍል።

7. ይህንንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል።”

8. ሌላው የምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ እንደየ ድርሻቸው ከፋፍሎ በመደበላቸው መሠረት፣ ራሱ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት ተቀበሉ።

9. ይህም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና በሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ እስከ ዲቦን የሚደርሰውን የሜድባን ደጋማ ምድር በሙሉ ይይዛል፤

10. እንዲሁም በሐሴቦን ተቀምጦ እስከ አሞናውያን ዳርቻ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል፤

11. በተጨማሪም ገለዓድን፣ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፣ የአርሞንዔምን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ ይይዛል፤

12. ይህም በአስታሮትና በኤድራይ ሆኖ የገዛውን በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት በሙሉ ያጠቃልላል፤ ዐግም በሕይወት ከቀሩት ከመጨረሻዎቹ ከራፋይም ዘሮች አንዱ ነበር፤ እነዚህንም ሙሴ ድል አደረጋቸው፤ ምድራቸውንም ያዘ፤

13. ነገር ግን እስራኤላውያን የጌሹርንና የማዕካትን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላቸው ይኖራሉ።

14. ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቊርባን፣ በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 13