ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 1:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ፣ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ አለው፤

2. “እነሆ፤ ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ እንግዲህ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሡ፤ ለእሥራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ።

3. ለሙሴ በሰጠሁትም ተስፋ መሠረት፣ እግራችሁ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ እሰጣችኋለሁ።

4. የርስታችሁ ዳርቻ ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከታላቁ ወንዝ ከኤፍራጥስ አንሥቶ፣ የኬጢያውያንን ምድር በሙሉ ይዞ፣ በምዕራብ በኩል እስከ ታላቁ ባሕር ይደርሳል።

5. በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ፤ ከቶ አልጥልህም፤ አልተውህም።

6. “ጽና፤ ለቀደሙት አባቶቻቸው እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር እንዲወርሱ፣ ይህን ሕዝብ የምትመራው አንተ ነህና በርታ።

7. አይዞህ፤ ብቻ አንተ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ የሰጠህን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።

8. ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም፤

9. በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”

10. ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤

11. “ወደ ሰፈር ግቡ፤ ለሕዝቡም፣ ‘ስንቃችሁን አዘጋጁ፤ ከአሁን ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ትወርሳላችሁ’ በሏቸው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 1