ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 63:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. የበቀል ቀን በልቤ አለ፤የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአል።

5. ተመለከትሁ፤ የሚረዳ ግን አልነበረም፤የሚያግዝ ባለመኖሩም ተገረምሁ፤ስለዚህ የገዛ ክንዴ ድነትን አመጣልኝ፤የገዛ ቊጣዬም አጸናኝ፤

6. መንግሥታትን በቍጣዬ ረጋገጥሁ፤በመዓቴም አሰከርኋቸው፤ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስሁ።”

7. የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ እግዚአብሔር ስላደረገልን ሁሉ፣ስለሚመሰገንበት ሥራው፣እንደ ፍቅሩና እንደ ቸርነቱ መጠን፣ለእስራኤል ቤት ያደረገውን፣አዎን፣ ስላደረገው መልካም ነገር እናገራለሁ።

8. እርሱም፣ “ርግጥ ነው፤ እነርሱ ሕዝቤ ናቸው፤የማይዋሹኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው” አለ።ስለዚህም አዳኝ ሆነላቸው።

9. በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ፤የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤በፍቅሩና በምሕረቱ ዋጃቸው፤በቀደመው ዘመን ሁሉ አነሣቸው፤ተሸከማቸውም።

10. እነርሱ ግን ዐመፁ፤ቅዱስ መንፈሱንም አሳዘኑ፤ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፤እርሱ ራሱ ተዋጋቸው።

11. ከዚያም ሕዝቡ የጥንቱን ዘመን፣የሙሴንና የሕዝቡን ጊዜ እንዲህ በማለት አስታወሱ፤የበጎቹን እረኛ፣ከባሕሩ ያወጣቸው እርሱ የት አለ?ቅዱስ መንፈሱንም፣በመካከላቸው ያኖረ እርሱ የት አለ?

12. የከበረው ኀያል ክንድ፣በሙሴ ቀኝ እጅ ላይ እንዲያርፍ አደረገ፤ለራሱ የዘላለም ዝና እንዲሆንለት፣ውሆችን በፊታቸው ከፈለ።

13. ፈረስ በምድረ በዳ እንደሚያልፍ ሁሉ፣እነርሱንም በጥልቁ ውስጥ አሳልፎ መራቸው፤ስለዚህም አልተሰናከሉም፤

14. ወደ ሸለቆ እንደሚወርድ የከብት መንጋ፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ዕረፍት ተሰጣቸው።ሕዝብህን በዚህ ሁኔታ የመራሃቸው፣ስምህን የከበረ ለማድረግ ነው።

15. ከተቀደሰው፣ ከተከበረውና ከፍ ካለው ዙፋንህ፣ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤ኀይልህና ቅናትህ የት አለ?ገርነትህና ርኅራኄህ ከእኛ ርቀዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 63