ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 60:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. የመቅደሴን ቦታ ለማስጌጥ፣የሊባኖስ ክብር፣ጥዱ፣ አስታውና ባርሰነቱ በአንድነት ወደ አንቺ ይመጣሉ፤እግሬ የሚያርፍበትንም ስፍራ አከብራለሁ።

14. የአስጨናቂዎችሽ ወንዶች ልጆች እየሰገዱ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤የናቁሽም ሁሉ እግርሽ ላይ ይደፋሉ፤ የእግዚአብሔር ከተማ፣የእስራኤል ቅዱስ ገንዘብ የሆንሽው ጽዮን ብለው ይጠሩሻል።

15. “የተተውሽና የተጠላሽ፣ማንም ሰው የማያልፍብሽ ብትሆኝም እንኳ፣እኔ የዘላለም ትምክሕት፣የትውልድም ሁሉ ደስታ አደርግሻለሁ።

16. የመንግሥታትን ወተት ትጠጫለሽ፤የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣ቤዛሽም እኔ የያዕቆብ ኀያል እንደሆንሁ ታውቂያለሽ።

17. በናስ ፈንታ ወርቅ፣በብረትም ፈንታ ብር አመጣልሻለሁ።ሰላምን ገዥሽ፣ጽድቅንም አለቃሽ አደርጋለሁ።

18. ከእንግዲህ በምድርሽ ሁከት፣በጠረፎችሽም ጥፋትና መፈራረስ አይሰማም፤ነገር ግን ቅጥሮችሽን ድነት፣በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያቸዋለሽ።

19. ከእንግዲህ በቀን የፀሓይ ብርሃን አያስፈልግሽም፤በሌሊትም የጨረቃ ብርሃን አያበራልሽም፤ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃን፣አምላክሽም ክብርሽ ይሆናልና።

20. ፀሓይሽ ከእንግዲህ አትጠልቅም፤ጨረቃሽም ብርሃን መስጠቷን አታቋርጥም፤ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናል፤የሐዘንሽም ቀን ያከትማል።

21. ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ፤ለክብሬ መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣የእጆቼ ሥራ፣እኔ የተከልኋቸው ቊጥቋጦች ናቸው።

22. ከአንቺ ታናሽ የሆነው ሺህ፣ከሁሉም የመጨረሻው ታናሽ ኀያል መንግሥት ይሆናል፤እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ጊዜውም ሲደርስ ይህን በፍጥነት አደርጋለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 60