ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 59:14-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቆአል፤ጽድቅም በሩቁ ቆሞአል፤እውነት በመንገድ ላይ ተሰናክሎአል፤ቅንነትም መግባት አልቻለም።

15. እውነት የትም ቦታ አይገኝም፤ከክፋት የሚርቅ ለጥቃት የተጋለጠ ነው። እግዚአብሔር ተመለከተ፤ፍትሕ በመታጣቱም ዐዘነ።

16. ማንም እንደሌለ አየ፤ወደ እርሱ የሚማልድ ባለመኖሩ ተገረመ፤ስለዚህ የገዛ ክንዱ ድነት አመጣለት፤የራሱም ጽድቅ ደግፎ ያዘው።

17. ጽድቅን እንደ ጥሩር አጠለቀ፤የድነትን ቊር በራሱ ላይ ደፋ፤የበቀልንም ልብስ ለበሰ፤መጐናጸፊያ እንደሚደረብም ቅናትን ደረበ።

18. እንደ ሥራቸው መጠን፣ቊጣን ለባላጋራዎቹ፣ፍዳን ለጠላቶቹ፣እንደዚሁ ይከፍላቸዋል፤ለደሴቶችም የእጃቸውን ይሰጣቸዋል።

19. በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም ይፈራሉ፤በፀሓይ መውጫ ያሉት ለክብሩ ይገዛሉ፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እንደ ተቋተ፣እንደ ተከማቸም ጐርፍ ይመጣልና።

20. “አዳኝ ወደ ጽዮን፣ኀጢአታቸውንም ወደ ተናዘዙት ወደ ያዕቆብ ቤት ይመጣል”ይላል እግዚአብሔር።

21. “በእኔ በኩል፣ ከእነርሱ ጋር ያለኝ ቃል ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “በአንተም ላይ ያለው መንፈሴ፣ በአፍህ ያስቀመጥሁት ቃሌ ከአፍህ፣ ከልጆችህ አፍ፣ ከዘር ዘሮቻቸውም አፍ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም አይለይም” ይላል እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 59