ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 52:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በመጀመሪያ ሕዝቤ ይኖር ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፤በኋላም አሦር ያለ ምክንያት አስጨንቆ ገዛው።

5. “አሁን እዚህ ምን አለኝ?” ይላል እግዚአብሔር፤“ሕዝቤ ያለ ምክንያት ተወስዶአል፤የገዟቸው ተሣልቀውባቸዋል”ይላል እግዚአብሔር።“ቀኑን ሙሉ፣ስሜ ያለ ማቋረጥ ይሰደባል።

6. ስለዚህ ሕዝቤ ስሜን ያውቃል፤በዚያ ቀንም፣አስቀድሜ የተናገርሁ እኔ መሆኔን ይረዳል፤እነሆ፤ እኔው ነኝ።”

7. በተራሮች ላይ የቆሙ፣የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣ሰላምን የሚናገሩ፣መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ድነትን የሚያውጁ፣ጽዮንንም፣“አምላክሽ ነግሦአል” የሚሉ እንዴት ያማሩ ናቸው።

8. ስሚ፤ ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገዋል፤በአንድነት በእልልታ ይዘምራሉ። እግዚአብሔር ወደ ጽዮን ሲመለስ፣በዐይኖቻቸው ያያሉ።

9. እናንት የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች፣በአንድነት በእልልታ ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአል፤ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቶአልና።

10. እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣የተቀደሰ ክንዱን ይገልጣል፤በምድር ዳርቻዎች ያሉ ሁሉ፣የአምላካችንን ማዳን ያያሉ።

11. እናንት የእግዚአብሔርን ዕቃ የምትሸከሙ፣ተለዩ፤ ተለዩ፤ ከዚያ ውጡ፤ርኵስ ነገር አትንኩ፤ከዚያ ውጡ ንጹሓንም ሁኑ።

12. ሆኖም በችኰላ አትወጡም፤ሸሽታችሁም አትሄዱም፤ እግዚአብሔር ፊት ፊታችሁ ይሄዳል፤የእስራኤል አምላክ ደጀን ይሆናችኋል።

13. እነሆ፤ ባሪያዬ የሚያከናውነው በማስተዋል ነው፤ገናና ይሆናል፤ ከፍ ከፍ ይላል፤ እጅግ ይከብራልም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 52