ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 5:21-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ራሳቸውን እንደ ብልኅ ለሚቈጥሩ፣በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው!

22. የወይን ጠጅ ለመጠጣት ጀግኖች፣የሚያሰክር መጠጥ ለመደባለቅ ብርቱ ለሆኑ ወዮላቸው!

23. ጒቦን በመቀበል በደለኛን ንጹሕ ለሚያደርጉ፣ለበደል አልባ ሰው ፍትሕን ለሚነፍጉ ወዮላቸው!

24. ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበናል፤የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃለዋል።

25. የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነዶአል፤እጁን አንሥቶ መቶአቸዋል፤ተራሮች ራዱ፤ሬሳዎችም በመንገድ ላይ እንደተጣለ ጥራጊ ሆኑ፤ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቍጣው ገና አልተመለሰም፤እጁም እንደ ተነሣ ነው።

26. ከሩቅ ያሉትን ሕዝቦች የሚጠራበትንምልክት ያቆማል፤ከምድር ዳርቻም በፉጨት ይጠራቸዋል፤እነርሱም እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ።

27. በመካከላቸው ደካማና ስንኩል አይገኝም፤የሚያንቀላፋና የሚተኛ አይኖርም፤የወገባቸው መቀነት አይላላም፤የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም።

28. ፍላጻቸው የተሳለ፣ቀስታቸውም የተደገነ ነው፤የሠረገሎቻቸውም መንኰራኵሮች እንደዐውሎ ነፋስ ናቸው።

29. ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣሉ፤ያደኑትንም ይዘው ይጮኻሉ፤ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ የሚያስጥልም የለም።

30. በዚያን ቀንእንደ ባሕር ሞገድ ይጮኹበታል፤ማንም ወደ ምድር ቢመለከት፣ጨለማንና መከራን ያያል፤ብርሃን እንኳ በደመናዎች ይጋረዳል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 5