ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 44:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ነገር ግን አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ፣የመረጥሁህ እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤

2. የፈጠረህ፣ በማሕፀን የሠራህ፣የሚረዳህ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ባሪያዬ ያዕቆብ፣የመረጥሁህ ይሹሩን ሆይ፣ አትፍራ።

3. በተጠማ ምድር ላይ ውሃ፤በደረቅ መሬት ላይ ወንዞችን አፈሳለሁና፤መንፈሴን በዘርህ፣በረከቴንም በልጅ ልጅህ ላይ አወርዳለሁ።

4. እነርሱም በለመለመ መስክ ላይ እንደ ሣር፣በወንዝ ዳር እንደ አኻያ ዛፍ ይበቅላሉ።

5. አንዱ፣ ‘እኔ የእግዚአብሔር ነኝ’ ይላል፤ሌላው ራሱን በያዕቆብ ስም ይጠራልሌላው ደግሞ በእጁ ላይ ‘የእግዚአብሔር ነኝ’ ብሎ ይጽፋል፤ራሱን በእስራኤል ስም ይጠራል።

6. “የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።

7. እስቲ እንደ እኔ ማን አለ? ይናገር፤ሕዝቤን ከጥንት ስመሠርት ምን እንደ ነበረ፣ገና ወደ ፊት ምን እንደሚሆን፣ይናገር፤ በፊቴ ያስረዳ፤ስለሚመጣውም ነገር አስቀድሞ ይናገር።

8. አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ይህን አልነገርኋችሁምን? ቀድሞስ አላሳወ ቅኋችሁምን?ለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ!ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።”

9. ጣዖት የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች፣የሚሰሩባቸውም ነገሮች ዋጋ ቢስ ናቸው፤የሚናገሩላቸው ዕውሮች ናቸው፤ዕውቀት የላቸውም ያፍራሉም።

10. ለምንም የማይጠቅመውን አምላክ የሚቀርጽ፣ጣዖትን የሚያበጅስ ማነው?

11. ጣዖት የሚሠራ ሰው እንጂ ሌላ አይደለም፤እርሱና መሰሎቹም ያፍራሉ፤ሁሉም ተሰብስበው በአንድ ላይ ይቁሙ፤ይደነግጣሉ፤ ይዋረዳሉም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 44