ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 40:16-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ሊባኖስ ለመሠዊያ እሳት አትበቃም፤የእንስሶቿም ቍጥር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያንሳል።

17. አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንደ ኢምንት ናቸው፤ከምንም የማይቈጠሩ መና ናቸው።

18. እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ?ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?

19. የተቀረጸውንማ ምስል ባለጅ ይቀርጸዋል፤ወርቅ አንጥረኛም በወርቅ ይለብጠዋል፤የብር ሰንሰለትም ያበጅለታል።

20. እንዲህ ያለውን መባ ማቅረብ የማይችል ምስኪን ድኻ፣የማይነቅዝ ዕንጨት ይመርጣል፤የማይወድቅ ምስልን ለማቆምም፣ታዋቂ ባለ ሙያ ይፈልጋል።

21. አላወቃችሁምን?አልሰማችሁምን?ከጥንት አልተነገራችሁምን?ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?

22. እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው።ሰማያትን እንደ ድባብ ይዘረጋቸዋል፤እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል።

23. አለቆችን ኢምንት፣የዚህን ዓለም ገዦች እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል።

24. ተተክለው ምንም ያህል ሳይቈዩ፣ተዘርተው ምንም ያህል ሳይሰነብቱ፣ገና ሥር መስደድ ሳይጀምሩአነፈሰባቸው፤ እነርሱም ደረቁ፤ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ጠራርጎ ወሰዳቸው።

25. ቅዱሱ፣ “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ?የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።

26. ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው?የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው።ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣አንዳቸውም አይጠፉም።

27. ያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ?እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ?“መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 40