ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 38:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “ ‘እግዚአብሔር የገባልህን ቃል እንደሚፈጽምልህ፣ የእግዚአብሔር ምልክት ይህ ነው፤

8. በአካዝ የሰዓት መቍጠሪያ ደረጃ ላይ፣ የወረደውን የፀሓይ ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።’ ” ስለዚህ ወርዶ የነበረው የፀሓይ ጥላ ያንኑ ያህል ወደ ኋላ ተመለሰ።

9. የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከተፈወሰ በኋላ የጻፈው ጽሕፈት፤

10. እኔ፣ “በዕድሜዬ እኩሌታ፣በሲኦል ደጆች ማለፍ አለብኝን?የቀረውንስ ዘመኔን ልነጠቅ ይገባልን?” አልሁ።

11. እንዲህም አልሁ፤ “ዳግም እግዚአብሔርን፣ እግዚአብሔርን በሕያዋን ምድር አላይም፤ከእንግዲህም የሰውን ዘር አላይም፤በዚህ ዓለም ከሚኖሩትም ጋር አልሆንም።

12. ቤቴ እንደ እረኛ ድንኳን ተነቀለ፤ከእኔም ተወሰደ፤ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፤ከመጠቅለያ ቈርጦኛል፤ከጠዋት እስከ ማታ ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

13. እስከ ማለዳ በትዕግሥት ጠበቅሁ፤እርሱ ግን እንደ አንበሳ ዐጥንቶቼን ሁሉ ሰባበረ፤ከጠዋት እስከ ማታም ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

14. እንደ ጨረባ፣ እንደ ሽመላም ተንጫጫሁ፤እንደ ርግብ አልጐመጐምሁ፤ዐይኖቼ ወደ ሰማይ በመመልከት ደከሙ፤ጌታ ሆይ፤ ተጨንቄአለሁና ታደገኝ።”

15. እንግዲህ ምን እላለሁ?እርሱ ተናግሮኛል፤ ራሱ ደግሞ ይህን አድርጓል፤ስለ ነፍሴ ጭንቀት፣ዕድሜዬን ሁሉ በትሕትና እሄዳለሁ።

16. ጌታ ሆይ፤ ሰዎች በእነዚህ ነገሮች ይኖራሉ፤መንፈሴም እንዲሁ በእነዚህ ሕይወትን ያገኛል፤ፈወስኸኝ፤በሕይወትም አኖርኸኝ።

17. እነሆ፤ በሥቃይ የተጨነቅሁት፣ለጥቅሜ ሆነ፤ከጥፋት ጒድጓድ፣በፍቅርህ ጠበቅኸኝ፤ኀጢአቴንም ሁሉ፣ወደ ኋላህ ጣልኽ።

18. ሲኦል አያመሰግንህም፤ሞት አያወድስህም፤ወደ ጒድጓድ የሚወርዱ፣የአንተን ታማኝነት ተስፋ አያደርጉም።

19. እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል።ስለ አንተ ታማኝነትም፣አባቶች ለልጆቻቸው ይነግራሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 38