ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 34:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እናንት አሕዛብ ሆይ፤ ኑ አድምጡም፤እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አስተውሉ።ምድርና በውስጧ ያለ ሁሉ፣ዓለምና ከእርሷ የሚበቅል ሁሉ ይስማ።

2. እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ ተቈጥቶአል፤ቍጣውም በሰራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ፈጽሞ ያጠፋቸዋል፤ለዕርድም አሳልፎ ይሰጣቸዋል።

3. ከእነርሱም የተገደሉት ወደ ውጭ ይጣላሉ፤ሬሳቸው ይከረፋል፤ተራሮችም ደም በደም ይሆናሉ።

4. የሰማይ ከዋክብት ሁሉ ይሟሽሻሉ፤ሰማይ እንደ ብራና ይጠቀለላል፤የከዋክብት ሰራዊት ሁሉ፣ጠውልጎ እንደ ረገፈ የወይን ቅጠል፣ደርቆም እንደ ወደቀ የበለስ ቅጠል ይሆናሉ።

5. ሰይፌ በሰማያት እስኪበቃት ጠጥታለች፤እነሆ፤ ወደ ኤዶም፣ፈጽሞ ወዳጠፋሁት ሕዝብ ለፍርድ ወርዳለች።

6. የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተነክራለች፤ሥብ ጠግባለች፤በበግ ጠቦትና በፍየል ደም፣በአውራም በግ ኵላሊት ሥብ ተሸፍናለች። እግዚአብሔር በባሶራ ከተማ መሥዋዕት፣በኤዶምም ታላቅ ዕርድ አዘጋጅቶአልና።

7. ጐሽ አብሮአቸው፣ኮርማም ከወይፈን ጋር ይወድቃል፤ምድራቸው በደም ትርሳለች፤ዐፈራቸውም ሥብ በሥብ ይሆናል።

8. እግዚአብሔር የበቀል ቀን፣ስለ ጽዮንም የሚሟገትበት ዓመት አለውና።

9. የኤዶም ምንጮች ሬንጅ፣ዐፈሯ የሚቃጠል ድኝ፣ምድሯም የሚንበለበል ዝፍት ይሆናል።

10. እሳቷ ሌሊትና ቀን አይጠፋም፤ጢሷም ለዘላለም ይትጐለጐላል፤ከትውልድ እስከ ትውልድ ባድማ ትሆናለች፤ማንም በዚያ ዳግም አያልፍም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 34