ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 9:22-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. የሚያከብሩበትም ምክንያት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍት ያገኙበት፣ ሐዘናቸው ወደ ደስታ፣ ልቅሷቸውም ወደ ክብረ በዓል የተለወጠበት ቀን ስለ ሆነ ነው። ቀኖቹንም የተድላና የደስታ ቀኖች አድርገው፣ እርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲያከብሩ ጻፈላቸው።

23. ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ለመፈጸምና የጀመሩትን በዓል ለማክበር ተስማሙ፤

24. ምክንያቱም የአይሁድ ሁሉ ጠላት የሆነው የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፤ ሊፈጃቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የተባለ ዕጣ ጥሎ ነበር።

25. ሤራው በንጉሡ ዘንድ እንደ ታወቀ ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ሤራ በገዛ ራሱ ላይ እንዲጠመጠም፣ እርሱና ወንዶች ልጆቹም በዕንጨት ላይ እንዲሰቀሉ የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ።

26. ስለዚህ እነዚህ ቀኖች ፉር ከሚለው ቃል “ፉሪም” ለመባል በቁ። በዚህ ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ሁሉ፣ ስላዩትና ስለ ደረሰባቸውም ነገር ሁሉ፣

27. አይሁድ በታዘዘውና በተወሰነው ጊዜ እነርሱና ዘሮቻቸው፣ እነርሱን የተጠጓቸውም ሁሉ እነዚህን ሁለት ቀኖች በየዓመቱ ባለማቋረጥ እንዲያከብሩ ሥርዐት አድርገው ራሳቸው ወሰኑ።

28. እነዚህም ቀኖች በእያንዳንዱ ትውልድ፣ በእያንዳንዱ ቤተ ሰብ፣ በእያንዳንዱ አውራጃና በእያንዳንዱ ከተማ መታሰብና መከበር ይኖርባቸዋል፤ ይኸውም እነዚህ የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ ሳይከበሩ እንዳይቀሩ፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል እንዳይደመሰስ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 9