ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 6:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚያች ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ መተኛት አልቻለም። ስለዚህ በዘመነ መንግሥቱ የተመዘገበው የታሪክ መጽሐፍ ቀርቦ እንዲነበብለት አዘዘ።

2. በዚያም በሩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ የጦር አዛዦች ሁለቱ፣ ገበታና ታራ ንጉሥ ጠረክሲስን ለመግደል አሢረው እንደ ነበርና ይህንንም መርዶክዮስ እንደ ተናገረ ተጽፎ ተገኘ።

3. ንጉሡም፣ “ታዲያ ይህን በማድረጉ መርዶክዮስ ያገኘው ክብርና ማዕረግ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።የቅርብ አገልጋዮቹም፣ “ምንም አልተደረገለትም” ብለው መለሱ።

4. ንጉሡም፣ “በአደባባዩ ማን አለ?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ሐማ በተከለው ዕንጨት ላይ መርዶክዮስ ይሰቀል ዘንድ ለንጉሡ ለመናገር በውጭ በኩል ወደሚገኘው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ገና መድረሱ ነበር።

5. የቅርብ አገልጋዮቹም፣ “እነሆ፤ ሐማ በአደባባዩ ቆሞአል” አሉት።ንጉሡም፣ “ግባ በሉት” ብሎ አዘዘ።

6. ሐማ በገባ ጊዜ ንጉሡ፣ “ንጉሥ ሊያከብረው ለወደደው ሰው ምን ሊደረግለት ይገባል?” ሲል ጠየቀው።በዚህ ጊዜ ሐማ፣ “ንጉሡ ከእኔ ይልቅ የሚያከብረው ማን አለ?” ሲል በልቡ ዐሰበ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 6